“አሁን የተመዘገበው የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ዕድገት ሀገሪቱ ግብርና መር ኢኮኖሚ ስትከተል ከነበረችብት ጊዜ እንኳን በብዙ መልኩ የላቀ ነው፡፡”ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶር)
ባሳለፈነው በጀት ዓመት የግብርና ዘርፍ 7 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት ያሰመዘገበ ሲሆን ከአጠቃላይ ዕድገታችን ዉስጥ ግብርና 2 ነጥብ 3 ድርሻ አለዉ፡፡
ከግብርና ምርት አንጻር ከሪፎርሙ በፊት በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሩዝ ምርት 1.5 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን ባለፈዉ ዓመት ግን 63 ሚሊዮን ኩንታል ሩዝ ማምረት ተችሏል። ይህ የሩዝ ምርት በኢኮኖሚዉ እድገት ዉስጥ ትልቅ ለዉጥ መኖሩን የሚያሳይ ነዉ፡፡
በተመሳሳይም የስንዴ ምርት ላይ ከፍተኛ ለውጥ የመጣ ሲሆን ከለዉጡ በፊት ኢትዮጵያ 47 ሚሊዮን ኩንታል ታመርት የነበረ ሲሆን ባለፈዉ ዓመት ግን ከ280 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ማምረት ተችሏል፡፡ ይህ ውጤት አሁን ላይ የግብርና ምርቶችን ከእጥፍ በላይ መጨመር መቻላችን ያመላከተናል፡፡
የቡና ምርትን በተመለከተም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስኬት ያመጣችበት ነው፡፡ ከለዉጡ በፊት የቡና ምርት 4.5 ሚሊዮን ኩንታል የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ኢክስፖርት የተደረገዉ ደግሞ 700ሺህ ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፈዉ ዓመት 11.5 ሚሊዮን ኩንታል ቡና አምርተናል፡፡
ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ የቡና ፍጆታ የሰዉ ቁጥር እያደገ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ እየጨመረ ቢሆንም ይህን ሁሉ ፍጆታ በመሸፈን 2.5 ቢሊዮን ዶላር ከዉጭ ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡
በጥቅሉ በግብርና ዘርፍ የተመዘገበው ዉጤትና ዕምርታ ግብርና መር ኢኮኖሚ እየተከተልን ነው ካልንበት ዘመን ጋር ሊወዳደር የማይችል ከፍተኛ ዉጤት የመጣበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለተመዘገበው ስኬት መላዉ አርሶ አደሮቻችንና የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎቻችን ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል ፡፡

