ከሳይበር ሥጋት ለመዳን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ንቃተ ህሊና መፍጠርና ማሳደግ ይገባል

ዓለማችን ዛሬ ትላንት የምናውቃት አይደለችም፡፡ ነገሮች በፍጥነት እየተለዋወጡ ቴክኖሎጂው እየፈጠነ ዓለም ውድድርና እሽቅድድም ውስጥ ገብታለች፡፡ ይህም ሆኖ አንዱ አንዱን ቀድሞ ለማለፍ በሚደረጉ ጥሩጫዎች ውስጥ ቴክኖሎጂውን ለመልካም የመጠቀሙ እድል እንዳለ ሆኖ ቴክኖሎጂ ለጥፋትም እየዋለ እንመለከታለን፡፡
በአሁኑ ወቅት በዓላማችን ላይ በርካታ የመሣሪያ ጦርነቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት እልባት ሳያገኝ የእስራኤልና የሀማስ ጦርነት ዓለምን እየፈተናት ይገኛል፡፡ በአፍሪካ ያሉት ግጭቶች በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ዜጎችን ፈተና ውስጥ ከቷቸዋል፡፡
ይህ በአይናችን የምንመለከተው የመሳሪያ የአካል ጦርነት ነው፡፡ የመሳሪያ እሽቅድድሙም የዚያኑ ያህል ጊዜ የሚሰጥ አልሆነም፡፡ በኪሎ ሜትሮች የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን ለማምረት የሚደረጉት ውድድሮች ዓላማችን ወደፊት ምን ይገጥማት ይሆን የሚለውን ስጋት እንዲያይል አድርጎታል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ለዓለም ፈተና እየሆነ የመጣው የሳይበር ጉዳይ የብዙ ሃገራት የደህንነት ስጋት ሆኗል፡፡ ሃገራት በማያውቁትና ባልጠበቁት ጊዜ በሳይበር የፋይናንስ ስርአታቸው ሲስተጓጎል፣መረጃዎቻቸው በመረጃ መንታፊዎች ገሃድ ሲወጡ እየተመለከትን ነው፡፡
ያለንበት ዘመን የእውቀትና የመረጃ ዘመን መሆኑ አይካድም፡፡ ሀገራት ከምንም በላይ ለእውቀት እና ለኢንፎርሜሽን ማህበረሰብ ግንባታ ቅድሚያ እየሰጡ እንመለከታለን፡፡ እውቀት ወደ ተግባር ሊለወጥ የሚችለው በመረጃ ላይ ሲመሰረት ነው፡፡ መረጃን በኢንፎርሜሽን በቴክኖሎጂ ታግዞ ተደራሽ ለማድረግ የመረጃውን ደህንነት የማረጋገጥ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመረጃ ደህንነት ስትራቴጂዎች ወሳኝ ይሆናል፡፡ የመረጃ ደህንነትን ለማረጋገጥ በርካታ ሃገራት የኢንፈፎርሜሽን ደህንነት አስተዳደር እና አሰራር ስርዓቶች ዘርግተው እየተገበሩ ይገኛል፡፡

ዘመኑ የደረሰበትን ደረጃ ለመግለጽ ዓለማትን የአንድ መንደር የመረጃ ቋት የቴክኖሎጂና ዲጂታል ኢንፎርሜሽን መሆኑ ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ በ2023 በዓለም ላይ 5 ነጥብ 3 ቢሊየን ሰዎች የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እንደሆኑ መረጃው ያሳያሉ፡፡ ይህ ማለት የዓለማችንን 65 ነጥብ 7 በመቶ ሕዝብ ማለት ነው፡፡
በኢትዮጵያም 20 ነጥብ 86 ሚሊየን ዜጎች የኢንተርኔት ተጠቃዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህ ማለት 16 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች የኢንተርኔት ተጠቃዎች ሆነዋል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ 6ነጥብ 40 ሚሊየን ዜጎች የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃዎች እንደሆነ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ይህንን ያህል መጠን የኢንተርኔት ተጠቃዎች ካሉ የመረጃ ስርጭትና ደህንነቱ ጉዳይ ሃገራትን በእጅጉ ሊያሳስባቸው እንደሚገባ ይታመናል፡፡ በሀገራችን የአንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ስርአት መስፋፋት ዜጎች ማንኛዉምን ዓለም አቀፍ መረጃን በቀላሉ ማግኘትና ማሰራጨትም እንዲችሉ እድል ፈጥሯል፡፡
ይሁን እንጂ የኢንፎርሜሽንና ዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋትን ተከትሎ በዓለም ላይ የተለያዩ ሰዎች የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት ቴክኖሎጂዉን በጠቀም በሀገራት ደህንነትና ሉዓላዊነት በተለይ በከፍተኛ ልማት ድርጅቶችና ፋይናንስ ተቋማት ላይ ጥቃት ሲፈፅሙና ለመፈጸም ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርጉ እንደሚስተዋል መረጃዎች በተደጋጋሚ ይገለጻሉ፡፡
በኢትዮጵያ የሳይበር ደንህነትን ተግባርና ዉጤታማ ለማድረግ የሳይበር ጥቃትን፤ ሙከራዎችና ስጋቶችን ለማስቀረት ሲባል 4ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር “አይበገሬ የሳይበር አቅም ለሀገር ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሀሳብ ተከብሯል፡፡ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሳይበር ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ጥናት ተደርጓል፡፡ በዚህ ጥናት መሰረት በሃገራችን ያለው የሳይበር ደህንነት እውቀት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን አመላክቷል፡፡
በያዝነው ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ 2 ሺህ 556 የሳይበር ጥቃት ሙከራ የተደረገ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁሟል፡፡ ይህ አሃዝ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ከተፈጸመው የሳይበር ጥቃት ሙከራ ጋር ሲነጻጻር በእጅጉ አድጓል፡፡
መንግስትም በበኩሉ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ከፍተኛ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ሳይበር ድንበር የለሽና ዉስብሰብ ወንጅል በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን በህዝብ ላይ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ንቃተ ህሊና መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡