የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለኢፌዴሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር የዕውቅና እና የምስጋና ስጦታ አበረከተ፡፡
መስከረም 20 ቀን 2018 ዓ/ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለኢፌዴሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር በ2017 ዓ/ም ጉባኤው የሠራቸውን የሰላም እና ማሕበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ለሕዝብ በስፋት ተደራሽ ይሆኑ ዘንድ በቂ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ ላበረከተው ሁሉን አቀፍ አገልግሎት በዛሬው ዕለት የዕውቅና እና የምስጋና ስጦታ በክብር አበርክቷል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸኃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰላምን በማጽናት፣ ግጭትን በመከላከል እና በመፍታት እንዲሁም በሕብረተሰቡ መካከል ያለውን የአብሮነት መስተጋብር ይበልጥ አጠናክሮ ከማስቀጠል አንፃር የሠራቸው ሥራዎች ሰፊ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ ከማድረግ አንፃር ሚኒስቴሩ የሰጠው አገልግሎት የላቀ መሆኑን በመግለጽ ለሚኒስቴሩ እና ለአመራሮቹ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም የጋራ በሆነው የሰላም ግንባታ እና ማህበረሰቡን በሚጠቅሙ ጉዳዩች ላይ ይበልጥ በመቀራረብ በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፤ ይበልጥ ተቀራርበን እና ተቀናጅተን እንሥራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት እናትዓለም መለስ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር በመንግስት እና በሕዝቡ መካከል ጤናማ እና እውነተኛ መረጃ እንዲኖር ማድረግ ኃላፊነቱ መሆኑን በመጠቆም ይህንን ኃላፊነቱን በተገቢው ሁኔታ ለመወጣት የሕዝብ ተቋም ከሆኑ፤ እንደ ኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ካሉ ተቋማት ጋር በመተባበር መሥራት አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተለይም እውነተኛ መረጃ ከማሰራጨት እና የሕዝብን ሰላም እና አንድነት ከማረጋገጥ አንፃር ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር ተቀራርቦ መሥራት ውጤታችንን ሊያሳድግልን ይችላል ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አክለውም ለሚኒስቴሩ ለተደረገው የዕውቅና እና የምስጋና ስጦታ ምስጋና አቅርበው በቀጣይም የተሻለ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ከበደ ዲሳሳ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር እውነተኛ እና ጤናማ በተለይም የሕዝብን ሰላም እና አንድነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ መረጃዎች ለሕዝቡ እንዲደርሱ ከማድረግ አንፃር በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቁመው በቀጣይም ይኸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹ ሲሆን ለተደረገው የዕውቅና እና የምስጋና ሥጦታም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ


