መንግሥት በመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማዉን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ ከሰሞኑ ባጋጠመው የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ በደረው ጉዳት የኢፌዴሪ መንግሥት የተሰማዉን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻል፡፡ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶችም መፅናናትን ይመኛል፡፡
ባጋጠመው አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ተጎጂዎች ለመታደግ፣ በናዳ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን ለማፈላለግ፣ የነብስ አድን ሥራዎችን ለማከናወን እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸዉን ዜጎች መልሶ ለማቋቋምና የደረሰውን የጉዳት መጠን ለመለየት ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ አስቸኳይ የአደጋ መከላከል ግብረ ኃይል በማቋቁም ወደ ስፍራው እንዲሄዱ አድርጓል፡፡ ግብረ ሃይሉም ከክልሉ መንግስትና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመቀናጃት ተጎጂዎችን ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
እስካሁን በአደጋው የ157 ሰዎች ህይወት የጠፋ ሲሆን ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱም ታውቋል።
የአደጋዉ የጉዳት መጠንና አጠቃላይ መረጃ በቀጣይ በተደራጀ መልክ የሚገለፅ ይኾናል፡፡መንግሥት ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትንና ብርታትን፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸዉ በቶሎ ማገገምን ይመኛል።
አስፈላጊዉን የመልሶ ማቋቋም ሥራ ከመሥራት ጎን ለጎን እንደዚህ ዓይነት አሳዛኝ አደጋ እንዳይከሰት የፌዴራል መንግሥት ከአካባቢው የመንግስት መዋቅር ጋር በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያከናውን ያሳውቃል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ
ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም