የዛሬ ትጋት ለነገ ትሩፈት ነው!

|

መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለጳጉሜ 5 የነገ ቀን እና ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ በሠላም አደረሳችሁ!

ነገ የጊዜ መቍጠሪያ ብቻ አይደለም፤ ነገ ተስፋ፣ ምኞት፣ ስንቅ፣ ለዛሬ መነሣሣትና ትጋት ምክንያት ጭምር ነው፡፡ ነገ ሁላችንም ለማየት የምንጓጓለት፣ የተሻለ ሕይወትና ስኬት እንዲኖረን የምንመኘዉ መሻታችን ነው፡፡

እንደግለሰብ የተሻለ ነገን እንመኛለን፤ እንደቤተሰብ የተሻለና የጋራ ደስታና ተድላ ያለው ነገን እናልማለን፤ እንደሀገር ሰላም፣ ደስታ፣ ብልጽግና እንዲኖረን በነገ ውስጥ እንጠብቃለን፡፡ ለዚህም ነው ባለፈው ትናንት ከመቆጨት ይልቅ በእጃችን ላይ ባለው ዛሬ ተመሥርተን ለነገ የምንተጋው፡፡ ለዚህም ነው አዲሱን ዓመት በጉጉትና በላቀ ተስፋና ተነሣሽነት የምንጠብቀው፡፡

ኢትዮጵያ ነገዋ ብሩህ ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት የኢትዮጵያን ነገ ለማቅናት በርካታ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

የተቋም ግንባታ ጅምሮቻችን ዘመን ተሻጋሪ መሠረት የያዙ ናቸው፤ በፀጥታ ተቋማት ተጀምሮ ወደሌሎችም የተሸጋገረዉ ሪፎርም የነገዋን ኢትዮጵያ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ የጀመርናቸዉ መርሐ ግብሮች ከዛሬ ባሻገር ናቸው፤ የነገው ትውልድ ምግቡን የሚለምን ሳይሆን አምርቶ ራሱን የሚመግብና አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲኖር ለማስቻል ነው፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ ሥራችን ነገም እንደትናንቱ አረንጓዴ የለበሰችና አብዛኛዉ ዛፎቿ የኢትዮጵያውያንን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ እንዲሆኑ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡ በትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ ዓልመዉ የተቃኙ ናቸው፡፡ ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ታዳጊዎችን እየመገብን ስናስተምር ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚሆኑ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት ነው፡፡ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የታሪክና ፖለቲካ ጨዋታ ቀያሪ ፕሮጀክቶችን የምንገነባዉ ለዛሬ የኃይል ፍላጎታችን ብቻ አይደለም፤ ያሏትን ጸጋዎች አልምተዉ የሚጠቀሙ ጀግኖች ኢትዮጵያ እንዳሏት ለማሳየት ብቻም አይደለም፤ ለነገው ትውልድ ኩራትና የይቻላል መንፈስን ለማውረስ ጭምር ነው፡፡

ዛሬ ሚሊዮን ኮደሮችን በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የምናሠለጥነው በነገና በቀጣዩ ትውልድ ላይ የላቀ ተስፋ ስላለን ነው፡፡ ዛሬ የሀገራችን ሉዓላዊነት ለማስከበርና ነፃ ሀገር እንደተረከብን ሁሉ ነፃ ሀገር ለማስረከብ የምንተጋዉ ነገም በራሱ የሚተማመንና በነፃነቱ የሚኮራ ትውልድ እንዲኖረን ስለምንሻ ነው፡፡

ከተሞቻችንን እያፈረስን የምንሠራው ነገን የሚመጥኑ እንዲሆኑና የላቀ ተስፋ የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡ ዛሬ ጥርሳችንን ነክሰን በርካታ ሪፎርሞችን የምንተገብረዉ ነጋችንን ለማሳመር ነው፡፡ በአጠቃላይ ነገ የዛሬ ውጤት ነው፤ ዛሬ ዐቅማችንን ሁሉ አሟጠን ከሠራን፣ ኃይላችንን ሁሉ አሰባስበን በችግሮቻችንና ፈተናዎቻችን ላይ ከተረባረብን ነጋችን ብሩህ ነው፡፡

ነገ አዲስ ዓመት ነው፤ ነገ በተስፋ የምንጠብቀዉ ብርቅ ዓመት ነው፡፡ ነገ የተሻለ እንዲሆን የተሻለ ዐቅደን እየጠበቅነው ነው፡፡ የነገ ሕይወታችን ከዛሬ ይሻላል፤ የነገ ቤተሰባችን ከዛሬ ይልቅ ያምራል፤ የነገ ከተሞቻን በብዙ መልኩ ከዛሬ ይሻላሉ፤ የነገ የገጠር መንደሮቻችን ሕይወት ከዛሬ በእጅጉ ይሻላል፤ የነገ ሀገራችን ከዛሬ የበለጠ ታምራለች፡፡

ለዚህም የእያንዳንዳችን አስተዋጽኦ ወሳኝ ነውና ለተሻለ ነገ የተሻለ ሐሳብ እናዋጣ፤ ለተሻለ ነገ ዛሬ የተሻለ ውጤት እናምጣ፡፡ ነገ የዛሬ ውጤት ነውና፡፡ ለዚህም ነው “የዛሬ ትጋት ለነገ ትሩፋት” በሚል መሪ መልእክት የዛሬዋን ቀን የምናከብራት፡፡

በድጋሜ እንኳን ለነገ ቀን አደረሰን፣ አደረሳችሁ፤ መልካም አዲስ ዓመት!

Similar Posts