ተኪ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ማምረት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ነዉ

የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም
መንግስት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለዉን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የሀገር ውስጥ ምርትን በበቂ ሁኔታ ለማሳደግ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።
በዚህም ባለፈዉ ዓመት ከአራት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል፡፡
የሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገት ዋና ማሳያ የምርት እድገት በመሆኑ፣ መንግስት በሂደት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አንዱ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እየሰራበት ነዉ፡፡ ለአብነትም በመጪዎቹ አምስት አመታት ዉስጥ በሁሉ የሀገሪቱ ወረዳዎች ዉስጥ አንድ ኢንተርፕራይዝ ለማቋቋም በእቅድ ተይዟል፡፡
የሀገሪቱን ምርት በማሳደግና ገቢዉ እንዲጨምር በማድረግ አዳዲስ የሥራ እድል እንዲፈጠር፣ የዜጎች ፍላጎት የሚያሟሉ ሸቀጦችና አገልግሎቶችን ማቅረብ ያስችላል፡፡ ይህ ሲሆን የዜጎች ኑሮ እየተሻሻለ፣ ድህነትም እየቀነሰ ይመጣል ማለት ነዉ፡፡
ኢትዮጵያም ሁሉንም ነገር አምርታ በራሷ መሸፈን የምትችልበት ሁኔታ አዳጋች ስለሆነ ምግብና ምግብ ነክ በተለይ ስንዴና ገብስ፣ መድሃኒት፣ የዘይት ምርቶችና የመሳሰሉ ስትራቴጂክ ምርቶች ላይ ራሷን ለመቻል በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
በተለይ እንደ ሀገር ያለንን አቅም መለየትና ገቢ ምርቶችን ለመተካት እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ምርቶቻችን ለመሸጥ ትልቅ ሚና ተጫዉቷል፡፡ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ ሰፊ የስራ እድል መፍጠርና ዜጎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችሉ እያደረገ ይገኛል።
ሀገሪቱ ለገቢ ምርቶች የምታወጣውን ወጪ ለመቀነስ ተኪ ምርቶችን በብዛት፣ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገበ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑ ነዉ፡፡