የሚዲያ ኢንዱስትሪዉ ወደ ዲጂታል እንዲሸጋገር ድጋፍ እየተደረገ ነዉ
የሚዲያ እንዱስትሪዉ በሂደት ወደ ድጂታል እንዲሸጋገር በመንግስት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በራሱ አቅም ያበለጸገውን የሞባይል መተግበሪያ (አፕ) በዛሬው ዕለት በይፋ አስመርቋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የኢቢሲ የሞባይል መተግበሪያ ማስጀመሪያ ዝግጀት ላይ ተግኝተዉ ባስተላለፉት መልዕክት፣ መንግስት የሚዲያ እንዱስትሪዉን ዐጠቃላይ ወደ የዲጂታል ሽግግር ለመዉሰድ ከፍተኛ ድጋፍ እየደረገ መሆኑን ገለጸው ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በፋይናንስና በቴክኒክ የተደረጉ ድጋፎችም ለዚህ ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡
የኢቢሲ የዲጂታል ሚዲያ ስራዎች ይበልጥ እንዲሳለጡ ከማድረግ አንጻር የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንስትቲዩት፣ እንዲሁም የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ቀዳሚ መሆናቸዉን በመጥቀስ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያላቸዉ፣ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የሚጣጣሙ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ባህል ጋር የሚሄዱ ይዘቶችን በጥራት፣ በአይነት፣ በመጠን እና በስፋት በማምረት በሁሉም አካባቢ በአንድ ወቅትና ጊዜ ማድረስ አስፈላጊ እንደሆነም ዶ/ር ለገሰ ጠቅሰዋል፡፡
በሚዲያ ስራ ዉስጥ የዜጎችን ግብረ መልስ መቀበል፣ የተገኘዉን ግብረ መልስ በመከተል የመረጃ ማሻሻያ እርምጃዎችን መዉስድ ይገባል ያሉት ዶ/ር ለገሰ በዚህ ረገድ ኢቢሲ ጥሩ የሆኑ ስራዎችን ጀምሯል በቀጣይም ይሄንን ስራ አጠናክሮ መሄድ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ መረጃ በከፍተኛ ፍጥነት ዓለምን ያዳርሳል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህ መተግበሪያ በየትኛዉም ዓለም የሚኖሩ ህዝቦች የሚከሰቱና የሚወሰኑ ጉዳዮችን ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ በማደረግ የተቀነባበሩና ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል አስተዋጽኦ እንዳለዉ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ አንጻር የዲጂታል ሚዲያዉ የሚያደርሰዉን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ሚዲያዎች ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚሄድ የተቀናጀና የተናበበ የዲጂታል ፕላትፎርም አማራጮችን በመፍጠር የሀገርን ሁለንተናዊ ገጽታ ለመጉዳት የሚረጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን መመከትና ማረም ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለባቸዉ አሳስበዋል፡፡
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላዉ በሰጡት አስተያየት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ኢቢሲ በራሱ አቅም ልዩ ዲጂታል መተግበሪያን ማበልፀጉ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው ተቋማት የአሁኑ እና የቀጣዩ ዘመን እውነታ የሆነውን ዲጂታላይዜሽንን በራሳቸው አውድ እውን ማድረግ እንደሚገባቸውም አጽዕኖት ሰጥተዋል፡፡
ዲጂታል ኢኮኖሚ እና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ባለፉት 7 ዓመታት በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህን ለማስቀጠል ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የሚል እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡



