የተዋሐደች እና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት በአፍሪካ ሕዝቦች መካከል ድልድይ መገንባትና ትስስር ማጠናከር ላይ መሥራት አለባቸው፡- ዶ.ር ለገሠ ቱሉ

ቀን-21-12-2017

የአፍሪካ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት የኅብረቱ አጀንዳ 2063 እንዲሳካ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ባህል ትስስር መጠናከር ላይ እንዲያተኩር የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ.ር) አሳሰቡ፡፡ 15ኛዉ የምሥራቅ አፍሪካ የኮሙኒኬሽን ማኅበር (East African Communication Association) ኮንፈረንስ አዲስ አበባ ላይ እየተካሄደ ነው፡፡

በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ.ር) “የተዋሐደች እና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የተግባቦት ሥራዉ የወል ትርክት መገንባት፣ ትምምን ማጠናከር፣ በአገራትና ሕዝቦች መካከል ጠንካራ የፖለቲካል-ኢኮኖሚ እና የባህል ውሕደት መፍጠር ላይ መሥራት ይገባዋል” ብለዋል፡፡

አህጉራዊና ቀጣናዊ ውሕደትን እውን ማድረግ የመሠረተ ልማት ትስስር፣ የተጠናከረ ቀጣናዊ መስተጋብር መኖር፣ የእርስ በርስ ትምምን መፈጠር፣ የባህል ልውውጥ መጠናከር አስፈላጊ መኾናቸዉን በንግግራቸዉ ያመላከቱት ክቡር ሚኒስትሩ “አስተሳሳሪ የወል ትርክት መገንባት፣ የጋራ ዕድል እና ዕጣ ፋንታ እንዳለን ማስገንዘብ፣ የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የወል ተስፋዎችንና ፈተናዎችን ማሳወቅ ከአህጉሩ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ይጠበቃል” ብለዋል፡፡

“የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የመረጃ አቅራቢ መዋቅር ብቻ አይደለም፤ የመግባባት መሠረት፣ የዐቅም ግንባታ አካል፣ የአካታች እና ሰላማዊ ማኅበረሰብ መቅረጫ መንገድ ጭምር ነው” ያሉት ዶክተር ለገሠ ይህንን ሚና በአግባቡ የሚወጣ አፍሪካዊ መሠረት እና ምልከታ ያለዉ ጠንካራ የሚዲያ ተቋምን አስፈላጊነትም በንግግራቸዉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እያስተናገደች ያለችው ኮንፈረንስ ከዚህ አንጻር ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት፣ ምሁራንና የዘርፉ ባለሙያዎች ዐዳዲስ ሐሳቦችን የሚያፈልቁበት እና ለአህጉራዊ ውሕደቱ የራሳቸዉን ዐሻራ የሚያሳርፉበት እንደሚኾንም ዶ.ር ለገሠ ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) በ36ኛዉ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካዊ ውሕደትን እውን ለማድረግ አህጉራዊ የሚዲያ ተቋም በመገንባት፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን ማጋለጥ፣ የወል አጀንዳዎችን ከፍ ማድረግ እና የአፍሪካ ድምፆችን አጉልቶ ማሰማት እንደሚገባ ማሳሰባቸዉን ያስታወሱት ዶ.ር ለገሠ እየተካሄደ ያለዉ ኮንፈረንስ ከዚህ አንጻር ሚናዉ የላቀ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ቤት እያስተናገደ የሚገኘዉ የምሥራቅ አፍሪካ የተግባቦት ማኅበር ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በኮንፈረንሱ ከአፍሪካ በተጨማሪ ከቻይና፣ አውሮፓ እና አሜሪካ የተውጣጡ የዘርፉ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች እና ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ነው፡፡

Similar Posts