ኢትዮጵያ ለማንሰራራት የሚስችላትን ከፍታ ይዛለች!
ኢትዮጵያ በሚመጥናት ከፍታ ልክ የሚያስቀምጣትን የማንሰራራት ጉዞ ጀምራለች፡፡ በጊዜ ምሕዋር ውስጥ ሲያጋጥሟት የነበሩ አንጋዳዎችን በብስለት እየተሻገረች ከፍታዋን በመያዝ ላይ ናት፡፡ የአይችሉም ትርክትን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሰብራለች፤ ብርሃንን ለምሥራቅ አፍሪካ ፈንጥቃለች፡፡
ያለማንም ዕርዳታ በኢትዮጵያውያን ሀብት፣ ድካም፣ ዕውቀትና ጥረት ሕዳሴን በማጠናቀቅ ኢንዱስትሪዎቿን በበቂ ታዳሽ ኃይል የምታንቀሳቀስ፣ ከዚያም አልፎ ለጎረቤት አገራት የምታጋራ ኾናለች፡፡ በውኃ ሀብቶቿ በፍትሐዊነት በመጠቀም ዐዲስ ልምድም ፈጥራለች፡፡
የቱሪዝም ኢንዱስትሪዋ በእጅጉ እየተለወጠ መጥቷል፡፡ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ሀብቶችን ከማስጎብኘት በመሻገር የኢትዮጵያን ከፍታ የሚመጥኑ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን አልምታለች፡፡ ከጎርጎራ እስከ ወንጪ፣ ከአላላ ኬላ እስከ ቤኑና፣ ከጨበራ ጩርጩራ እስከ ንጋት ሐይቅ ዐዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ኾነዋል፡፡ ነባር ከተሞቿ ዘምነው የቱሪስቶችን ቆይታ ከማራዘም ባሻገር ጠሪ እና ማራኪ ኾነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ለዘመናት ከነበረበት ከእጅ ወደ አፍ ወጥቶ ወደ ገበያ ተኮርና ትርፍ ምርት እየተሸጋገረ ነው፡፡ ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ዓመቱን ሙሉ ወደማምረት ተገብቷል፡፡
በሌማት ትሩፋት እና አረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄዎች የተገኙ ልምዶች የኢትዮጵያን ሥርዐተ ምግብ በማዘመን ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ የንብ ማነብ፣ የዶሮ እርባታ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በመሠረታዊነት ተለውጠው ከአርሶ አደሩ ባሻገር የከተሜዉ ሥራ ጭምር ተደርገዋል፡፡
የማዕድን ሀብቶቻችን በስፋት እና በሕጋዊ መንገድ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፡፡ እንደ ወርቅ ያሉ ውድ ሀብቶች ከሕገ ወጥ ግብይት ወጥተዉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረት እየኾኑ ነው፡፡ እንደ ኦፓል፣ የደንጋይ ከሰል፣ ብረት እና መሰል የማዕድን ሀብቶችን በስፋት የማምረትና የመጠቀም ልምድ እያደገ ነው፡፡ የእነዚህ ኹሉ ድምር ውጤት ኢትዮጵያ በሚመጥናት ከፍታ ለመቀመጥ እያንሰራራች መኾኑን ነው፡፡
እነዚህን ስኬታማ ጅምሮች አጠናክሮ መቀጠል፤ ዐዳዲስ እና አሻጋሪ ሐሳቦችን መፍጠር፤ የተፈጠሩ አሻጋሪ ሐሳቦችን መተግበር፤ ክፍተቶችን በቶሎ ማረም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ የሰው ሀብታችንን ማንቃት፣ ማብቃት፣ በአግባቡ ማሰማራት እና መምራት ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ነው “ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሰራራት” በሚል መሪ መልእክት ጳጉሜን 4፣ የማንሰራራት ቀንን፣ እያከበርን የምንገኘው፡፡
እንኳን ለጳጉሜን 4፣ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ቀን አደረሳችሁ!
ጳጉሜን 4/2017 ዓ.ም