“ኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብን በራስ ዐቅም ገንብታ ማጠናቀቋ ለአፍሪካ ሌላ ዐዲስ ምዕራፍ ነው፡፡” የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኞችና የቀድሞ የፍሪካ መሪዎች ቤተሰቦች
ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ የቀድሞ ፓን-አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ መሪዎች ቤተሰቦች እና ጋዜጠኞች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት በሰጡት አስተያየትም “ኢትዮጵያ ፓን አፍሪካኒዝምን በላቀ መሠረት ላይ ገንብታዋለች፤ ይህ ለአፍሪካ ሌላ ዐዲስ ምዕራፍ ነው” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያውያን በራስ ዐቅም እና ጥረት የተገነባዉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከዓድዋ ድል እና ከአፍሪካ ኅብረት ምሥረታ ቀጥሎ ሦስተኛዉ የፓን አፍሪካኒዝም መሠረት ተብሎ ሊወሰድ እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አስገራሚ የኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት ውጤት ነው፤ አፍሪካውያን ከምን ተነሥተውና እንዴት በራሳቸዉ ዐቅም መልማት እንደሚችሉ ያሳየ ነው ብሏል። ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴ ግድባቸዉ የማንንም የገንዘብ ድጋፍ አልጠበቁም፤ በራሳቸው ሠርተው ለዓለም ማሳየቷን ተናግሯል፡፡
ያለኢኮኖሚ ነፃነት ፖለቲካዊ ነፃነት ሊረጋገጥ እንደማይችል ያመለከቱት ጎብኚዎቹ “ሕዳሴ ለኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን አብሮ የመልማት እንጅ የመከፋፈል አጀንዳ ሊኾን አይገባም፡፡ ድሮ ስለሕዳሴ የሚጣረሱ መረጃዎችን እንሰማ ነበር፤ በጉብኝቱ ግን የነበረን ብዥታ አጥርተናል፤ በዐይናችንም ዐይተናል በማለት ጎብኝዎቹ ተናግሯል፡፡ “ግድቡ የፓን-አፍሪካኒዝም ሌላ ምሣሌ ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
የቀድሞዉ የዛምቢያ የነፃነት ታጋይና ፓን-አፍሪካኒስት ፕሬዝዳንት ኬኔት ካውንዳ ልጅ ካወች ካውንዳ እንተናገሩት “ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያውያን ባሻገር ሌሎች ጎረቤት አገራትን የሚጠቅም በራስ ዐቅም የተሠራ ፕሮጀክት ነው፡፡ በራስ ዐቅም መሠራቱ ብቻ የሚያስተምረው ነገር ብዙ ነው” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ጎረቤት አገራትን በታዳሽ ኃይል እያስተሳሰረች እና የፓን-አፍሪካኒዝም ዕሳቤን እየገነባች እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡ “ድንበሮቻችን የኛ አይደሉም፤ ቅኝ ገዥዎች የሠሯቸዉ ናቸው፤ ኢትዮጵያ ይህንን ድንበር በማለፍ አብሮ የመልማት መንገድን እየተከተለች ነው፤ ይህ ደግሞ ለሌሎችም ምሳሌ ነው” ሲሉም ካወች ካውንዳ የአባታቸው የአፍሪካ ነፃነትና አንድነት ሕልም ጥልቅ መሠረት እየያዘ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የጋናው የቀድሞ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ አንድነት አቀንቃኙ ኩዋሜ ንኩርማህ ልጅ ሳሚያ ንኩርማህም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉብኝት ካደረጉት መካከል ናቸው፡፡ “ኢትዮጵያውያን በጋራ ችለዋል፤ ተአምር ሊባል የሚችል እውነታ ፈጥረዋል፤ ይህንን ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ልምድ ሊወስዱበት ይገባል፡፡ በተመለከትኩት ነገር ብቻ ሳይኾን ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን ርብርብ ስረዳ ተገርሜያለሁ፡፡ አፍሪካ ውስጥ ዐዲስ አስተሳሰብ እየዳበረ ነው” ብለዋል፡፡
የአፍሪካ የቀድሞ የፓን-አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ መሪዎች ልጆች በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎችን እየጎበኙ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም አፍሪካን ለኢኮኖሚ ነፃነት አብነት ኾና እየመራች እንደምትገኝና በአስደናቂ የለውጥ ምሕዋር ላይ እንዳለች ተናግረዋል፡፡
በጉብኝቱ ፣ የጁሊዬስ ኔሬሬ፣ ፓትሪስ ሉሙምባ እና የሌሎችም የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎች ልጆች ተሳትፏል፡፡








