ሀገራዊ የልማት እቅዱ የተገኙ እምርታዊ ዉጤቶችን የሚያስቀጥልና የተደመረ አቅምን የሚፈጥር ነዉ- ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

የ2018 ሀገራዊ የልማት አቅድ በሁሉም ዘርፎች የተገኙ እምርታዊ ዉጤቶችን የሚያስቀጥልና ለላቀ ዉጤት የተደመረ አቅም የሚፈጥር እቅድ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ የአገልግሎቱ አመራርና ሰራተኞችም በእቅዱ ላይ ዛሬ ዉይይት አድርገዋል፡፡

የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ሀገራዊ እቅዱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም በሁሉም ዘርፎች ያስመዘገበችዉ የኢኮኖሚ እድገት እምርታ የታየበት መሆኑን ገለጸዋል፡፡ በኤክስፖርት ብቻ 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መድረሱን በምሳሌ የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትሩ፣ በግብርናም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን፣ እንዲሁም ዐጠቃላይ የፌዴራል መንግስት ገቢ 1 ነጥብ 2  ትሪሊዮን ብር መድረሱን አዉስተዋል፡፡  

በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት በርካታ የመንግስት አገልግሎቶች ወደ ድጂታል እንዲቀየሩ ተደርገዋል ያሉት ዶ/ር ለገሰ፣ ይህ ተጠናክሮ የሚቀጥልና  የመልካም አስተዳደር ችግርችን በዘላቂነት የሚፈታ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በፋይናንስ፣ በኢንዱስትሪና በሌሎች ዘርፎች የተመዘገቡ ዉጤቶች አጠቃላይ ለሀገሪቱ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸዉንም አንስተዋል፡፡

መንግስት በሀሳብ የበላይነት ላይ ተመስርቶ የተቆጠረ እቅድ በማዉጣና ተግባራዊ በማድረጉ፣ የወል ትርክት በማስረጹና የተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራቱ አስደማሚ የኢኮኖሚ ዉጤቶች ሊገኝ ችለዋል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ሀገራዊ የልማት ስራዎችን በተፈጠነና ጥራትን በጠበቀ ሁኔታ የማስቀጠል ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ 

በመጪዉ ዓመት ሰፋፊ የልማት እቅዶች መታቀዳቸዉን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ማዳበሪያ በሀገር ዉስጥ ለማምረት የሚያስችል ፋብሪካ መገንባት መጀመሩ፣ ድፍድፍ ነዳጅ በበቂ ሁኔታ ማምረትና ለገቢያ ማቅረብ፣ አዳዲስ የአምራች እንዱስትሪዎችን ምርት ዉስጥ ማስገባት፣ ዜጋ ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን መጀመርና ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር፣ የኑሮ ዉድነቱን መቀነስና እንደ ሊትየም ያሉ አዳዲስ የማዕድን ምርቶችን ለገቢያ ማቅረብ ዋና ዋና መሆናቸዉን አብራርተዋል፡፡

Similar Posts