“መታወቂያ ማግኘት የዜጎች መብት ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ መብት ነው”

ዓለም አቀፍ “የመታወቅ ቀን” በመስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡
መታወቂያ ማግኘት የዜጎች መብት ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ መብት እንደመሆኑ መሠረታዊ አገልግሎትን ለማግኘት ፥ መብትን ለማስጠበቅ እና በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ፣ሁሉም ሰው መታወቅ ይገባዋል፣ሁሉም ሰው የመታወቅ መብት አለው።
እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 16 ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፍ “የመታወቅ ቀን” ዘንድሮ በኢትዮጵያ በመስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም በዲጂታል መታወቂያ በተመለከተ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ፣ የ“ፋይዳ” ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አስፈላጊነት፣ የዜጎችን ተጠቃሚነትና መብቶችም መረጃ በመስጠት እየተከበረ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የመታወቅ ቀንን ስታከብር ዜጎችን ለዲጂታል መታወቂያ በማብቃት፣ አገልግሎቶችን በማሳደግ እና በኢኮኖሚ እድገት ላይ ያለውን ሚና በማሳየት ቁጥርኛ በመሆንዋ በአፍሪካ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ቀዳሚ አድርጓታል።
የዘንድሮው ዓመት የመታወቅ ቀን “ግለሰብ እና ማህበረሰብን የሚያበቃ፣ ሁሉንም አካታች የማንነት ስርዐት አስፈላጊነት አጉልቶ የሚያሳይ” ነው።
ከመስከረም 6 እስከ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ቀናት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በመላው አገሪቱ ቁልፍ ቦታዎች ላይ ከሚደረገው የፋይዳ የዘመቻ ምዝገባ ጎን ለጎን የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመሆን የኦንላይን ስርጭቶች ፥ የምዝገባ እንቅስቃሴዎች ጨምሮ የተለያዩ ተከታታይ ዝግጅቶችን ይከናወናሉ፡፡
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት እስካሁን ወደ 10 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎችን የመዘገበ ሲሆን፤ የመታወቅ ቀንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቁልፍ ፕሮጀክት የሆነውን በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ነዋሪዎቿ እንዲመዘገቡ የንቅናቄ ሥራዎች የሠራሉ፡፡
