መንግሥት በሁሉም መስኮች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል!
መጋቢት 1/2018 ዓ.ም
ባለፉት ሀምሳ ዓመታት የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍፁም መገለል ተነስተዉ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በልማት መስኮች የባለቤትነት ዋስትናን አረጋግጠዋል፡፡ ዛሬ ላይ ሴቶች በሀገሪቱ የፖለቲካ ዐዉድና ልማት ዘርፎች ውስጥ ግንባር ቀደም ሚናን እየተጫወቱም ይገኛሉ፡፡
ይህ ለውጥ የሴቶችን መሠረታዊ መብቶች ከማስጠበቅ ባለፈ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ገጽታ ላይ የሚታዩ ውጤቶችን እንዲጎናጸፉ አስችሏቸዋል፡፡
ሴት መሪዎች ፖሊሲዎችን በመቀረጽ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሳለጥ፣ ልማትን በማፋጠን፣ እንዲሁም ሰላምና ጸጥታን በማረጋገጥ ረገድ ተጨባጭ ለዉጦችን እያስመዘገቡ ይገኛል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ የሚታወሰው የዘንድሮ የሴቶች ቀን፣ “የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በአገልግሎቱ አመራርና ሠራተኞች ተከብሯል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ የሴቶች ቀን ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለሰዉ ልጆች ሁሉ ትልቅ ትርጉም ያለዉ በመሆኑ የሴቶችን መብት ለማስከበር መነሻ የሆኑ ንቅናቄዎችን ማስታወስና ድጋፍ ማድረግ የሁሉም ድርሻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሴቶች በዘመናት መካካል ባደረጉት ትግል የታላላቅ ስኬቶች ባለቤት መሆን ችለዋል ያሉት አቶ ከበደ መንግሥት የሴቶችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ አቅም በማሳደግ በዲሞክራሲዊ የምርጫ ሄደት የጎላ ተሳትፎቸውን ለማረጋገጥ የሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው በሁሉም መስኮች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የመንግሥት ቁርጠኝነት ጠንካራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ የሴቶች ተሳትፎ በፖለቲካና ሌሎችም መስኮች እድገት እያሣየ ቢሆንም ከሚፈለገው አንጻር ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚቀሩ አንስተዋል፡፡ በተለይ በየደረጃዉ ያሉ መዋቅሮች ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ከማድረግ አንጻር ውስንነት ያለበት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የሴቶችን ዐቅም ማጎልበትና ተሳትፎ ማሳደግ የችሮታ ጉዳይ ሳይሆን ግማሽ የማኅበረሰብ ክፍልን የማካተት ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዉ፣ ይህም ሁሉን አቀፍ ተሳትፎን፣ ዲሞክራሲንና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ዋስትና እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የሴቶች ቀንን በማስመልከት በሴቶችና ማኅበራዊ ሚኒስቴር የተዘጋጀዉ የመወያያ ሰነድ በፌዴራል ተቋማት ክትትልና ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ በአቶ እንዳለዉ ሙሉዓለም ቀርቦ ዉይይት የተደረገበት ሲሆን ተሳታፊዎቹ ዝግጅቱ ለሴቶች ሁለንተናዊ ጥንካሬ ትርጉም ያለው እና እንደሀገር እየተመዘገበ ባለው ስኬት የነቃ ተሳተፍ እንዲኖር የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication











