መንግስት የኢትዮጵያን የእዳ ቀንበር መሰበር ችሏል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግስት በወሰዳቸዉ ጠንካራ የሪፎርም ስራዎች ምክንያት ሀገሪቷ ላይ የነበረዉ የእዳ ቀንበር መስበር መቻሉን የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ የመንግስትን የ2017 እቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸዉ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም በአራት ዓመት ጊዜ ዉስጥ ኢትዮጵያ ላይ የነበረዉን የ3.5 ቢሊዮን ዶላር የብድር መጠን ሙሉ በሙሉ መነሳቱንን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ የማሰንራራት ዘመን ላይ መድረሷን አመላካች ነዉ ብለዋል፡፡ ለተገኘውም ስኬት ምክር ቤቱንና ሰፊውን ህዝብ አመስግነዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም ከዚህ ቀደም የነበሩ መንግስታት 3.5 ቢሊዮን ዶላር ተበድሮ ወደ እኛ ተሸጋግሮ የነበረዉን ትልቅ እዳ ወደ ቀጣዩ ትዉልድ እንዳይሸጋገር ዉጤታማ ስራዎች መሰራታቸዉን አዉስተዋል፡፡ ይህ በጥቂት ዓመታት ጊዜ ዉስጥ በእዳ ጫናዎች ቀይ የነበረዉን የኢትዮጵያን ገጽታ መቀየር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ተረጂ የነበሩ 23 ሚሊዮን ዜጎች እንዲቀነስ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም መንግስት የምግብ ለዓላዊነትን ለማረጋገጥ አበረታች ስራዎች መሰራታቸዉን፣ በዚህም አመርቂ ዉጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

በባለፈው ዓመት ብድርና እርዳታን ጨምሮ ከሁሉም የውጪ ምንዛሬ ማግኛ ምንጮች የተሰበሰበው ሀብት 24 ቢሊየን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓመት ብቻ ከኤክስፖርት የተገኘዉ ሀብት ብቻ 32 ቢሊየን ዶላር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ገቢን በሚመለከት ዘንድሮ ከግብር 900 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቦ አንድ ነጥብ ሁለት ትርሊዮን ወጪ መውጣቱን ተናግረዋል፡፡ በዲጂታል ፋይናንስ፣ በትራንስፖርትና በአገልግሎት ዘርፎች ጥቅል እድገት ታይተዋል ያሉት ጥቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከወጪ ንግድ ብቻ 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አንስተዋል፡፡ የወርቅ ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ረገድም ጥሩ እንቅስቃሴ የነበረ ሲሆን፣ እስካሁን 300 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አንስተዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት የ8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት 8 ነጥብ 4 እድገት ለማስመዝገብ ታቅዶ እየተሰራ መቆየቱንም አስታዉሰዋል፡፡

Similar Posts