መገናኛ ብዙሃን በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችንና አዳዲስ የምርምር ስራዎችን በተገቢው መልኩ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለጸ።

|

መገናኛ ብዙሃን በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችንና አዳዲስ የምርምር ስራዎችን በተገቢው መልኩ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለጸ።

መንግስት የሃገሪቱን ሰላምና ደህንነት ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ትልቁ ትኩረቱ ምርታማነትን ማሳደግ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ሙሉ ትኩረቱን ወደ ልማት እንዲመልስ ለማድረግ የመገናኛ ብዙሃን የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ፡፡

ዛሬ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮችና የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች፤ አርታኢዎችና ባለሙያዎች የግብርና ሚኒስቴር በሳይንስ ሙዚየም ያዘጋጀውን የግብርና ሳይንስ ኤግዚቢሽን ጎብኝተዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት በግብርና ዘርፍ ላይ አዳዲስ የምርምርና የፈጠራ ውጤቶች ያሏቸውን ወጣት ባለሙያዎች በማስተዋወቅና እውቅና በመስጠት ሚዲያዎች ዘርፉን የማዘመኑን ጥረት ሊያግዙ ይገባል።

የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን በሃገሪቱ እየተሳኩ ያሉ የልማት ውጤቶችን ሕብረተሰቡ እንዲያውቃቸው ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡ የግብርና ዘርፍ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተጨባጭ ለውጦችን አምጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግሩ በፍጥነት እየተጓዘ፤ ዘርፉ በምታማነትም በቴክኖሎጂ አጠቃቀምም የሚታይ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ዓመታት በጦርነትና በግጭት የጠፉትን ጊዜያት ለማካካስ ሙሉ አቅምን ለልማት ማዋል

እንደሚገባ፤ ይህ ኤግዚቢሽን ሲዘጋጅም አንዱ ዓላማው መንግስት ፊቱን ወደ ልማት መመለሱን ለማስገንዘብ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ በጥቂት ምርቶች ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረው የኤክስፖርት ምርት ዛሬ በፍራፍሬ እና በሌሎች ምርቶችም ማስፋት መቻሉን አንስተው የእነዚህ ተግባራት መረጃ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲደርስና የተሳትፎ መጠኑንም ከፍ ለማድረግ መገናኛ ብዙሃን ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

ለሚዲያ አመራሮችና ባለሙያዎች ገለጻ ያደረጉት የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ግብርናው ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘቱን ጠቅሰው ይህንን ዘርፍ ማሳደግ ማለት አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱን በአስተማማኝ ደረጃ ማስቀጠል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኤግዚቢሽኑ ሚያዚያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተከፍቶ ለአንድ ወር ክፍት ሆኖ የሚቆይ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ የደረሰችበትን ደረጃና ቀጣይ እቅዶቿን መጥቶ እንዲጎበኝ ጥሪ ቀርቧል።

Similar Posts