ሚዲያዉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞችና የመዳረሻ ትልሞች እንዲገነዘብ የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ ነው፡፡..

|

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት “ብሔራዊ ጥቅሞቻችንና የሚዲያ ሚና” በሚል ጭብጥ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ለሚዲያ ዋና አዘጋጆች፣ ምክትል ዋና አዘጋጆችና ከፍተኛ ባለሙዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡


የአገልግሎቱ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር አቶ ከበደ ዴሲሳ በሥልጠናዉ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ሥልጠናዉ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙዎች ስለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞችና የመዳረሻ ትልሞች የወል መረዳት እንዲኖራቸዉ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
“የሀገራዊ ገዥ ትርክት ግንባታ ምንነትና የሚዲያ ሚና” በሚል ርእስ ሥልጠና እየሰጡ የሚገኙት የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዐት ግንባታ ማእከል ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ ደግሞ ኢትዮጵያ ብዝኃነትንና አንድነትን በማዋሐድ ብሔራዊነትንና ዐርበኝነትን ማእከል ያደረገ ትርክት ግንባታ ላይ እንደምትገኝና ለዚህም ሚዲያዉ ጉልህ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡
ሚዲያ ትርክትን የማስረጽ ዐቅሙን ተጠቅሞ ፍጹማዊ አንድነትና ፍጹማዊ ልዩነት ላይ ከማተኮር ይልቅ አካታች የወል ትርክት ላይ በመቆም ብዝኃነትንና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጽናት እንዲተጋም አስገንዝበዋል፡፡
ሥልጠናዉ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞችና የሚዲያ ሚና፣ የኢትዮጵያ የሚዲያ ዓውድ እና የኢትዮጵያ የሚዲያ አፈጻጸም ምልከታ” በሚሉ ሌሎች ይዘቶች ላይ አተኩሮ በቀጣይ ቀናትም ይቀጥላል፡፡


በሥልጠናዉ ከ25 በላይ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተውጣጡ ዋና አዘጋጆች፣ ምክትል ዋና አዘጋጆችና ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም ከኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንና ከአገልግሎቱ የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳፉ ነው፡፡ አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ 200 ለሚደርሱ የሚዲያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች መሰል የዐቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡

Similar Posts