ምክክር ለጋራ አሸናፊነት፣ ምክክር ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረመንግሥት ግንባታ! – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ታኅሣሥ 24/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ለዘመናት ያለመግባባትና የንትርክ እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭት ምንጭ የነበረው ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችን የወለደው ችግር ነው። ይህን ችግር በመሠረታዊነት ለመቅረፍ እና በሀገራዊ ጉዳዮችና በብሔራዊ አጀንዳዎች ዙርያ የሚታዩ ልዩነቶችንና መካረሮችን ለማረቅ ሀገራዊ ምክክር ወሳኝ ጉዳይ ነው ፡፡
መንግሥት አዎንታዊ የሰላም ባህል እንዲሰፍንና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ተገንብቶ ኢትየጵያውያን ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙርያ በሃሳብ አውድ ብቻ መፍታት አለባቸው የሚል ፅኑ እምነት አለው፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ የተጀመረው ሁሉ አካታች የሆነ ሃገራዊ ምክክር ልዩነቶቻችንን በሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያገኘነው የማይተካ ዕድል ነው፡፡ ይህ ዕድል ለሁሉም አካላት የተከፈተ የትኛውንም ወገን የማይለይ የምክክር ዕድል ነው፡፡ በዚህ እድል ለመጠቀም ኢትዮጵያውያን ዝግጁ ልንሆን ይገባል፡፡
ይህ ዕድል የኖረውን የወንድማማችነት ዕሴት ያዳከመውን የተበላሸ የፖለቲካ ባህላችንን ከማከም ባለፈ ዘላቂ ሰላማችንን ለማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው።
የምክክር ዕድሉ በመሰረታዊ ጉዳዮቻችን ዙርያ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር ፣እየዳበረ የሚሄድ የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት፣ በመሃከላችን የእርስ በእርስ መተማመንን በመፍጠር እና የህዝቦችን መተባበርና አንድነት በማረጋገጥ የማይተካ ሚና ይኖረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ጦርነትና አብዮት የተሟላ መፍትሔ የማያመጡ መሆናቸውን በተግባር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በሁለቱም መንገድ የመጣ አሸናፊነት ጊዜያዊና መልሶ ቁርሾና ቂምን የሚያሳድር መንገድ መሆኑን በተግባር ተምረንበታል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በውይይትና በምክክር ችግሮቻቸውን አለመግባባቶቻቸውን የመፍታት ድንቅ ባህል የነበራቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ እሴት እየጎለበተ በመጣው ኋላቀር የፖለቲካ ባህል ምክንያት ከጊዜ ወደጊዜ በመደብዘዝ ከፋፋይ ነጠላ ትርክት መገለጫችን እስከመሆን ደርሷል፡፡
በአለም ላይ በርካታ ሀገራት ከከረረ ልዩነትና ከግጭት ድባብ ለመውጣት ሀገራዊ ምክክር እንደመፍትሄ ተጠቅመዋል፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ይህንን ማድረግ የማይሳነን ሕዝቦች ለመሆናችን በየአካባቢው ያሉ ባህላዊ ዕሴቶቻችን ማሳያ ናቸው፡፡
ስለሆነም ዘላቂ የሆነ መፍትሔን ለማምጣት በእውነተኛ ፖለቲካዊ መሻት በቅንነት ለውይይት ለሰጥቶ መቀበልና ለጋራ መፍትሔ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት መነሳት ይኖርበታል፡፡
ኢትዮጵያውያን የመጣንበት የግጭትና የጦርነት አዙሪት በቃን የምንልበት ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው፡፡ ግጭት ማንንም አሸናፊ የማያደርግ የጥፋት አዙሪት ስለሆነ የሀገራዊ ምክክር ሂደትን ስኬታማ ማድረግ ፣ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ የህግ የበላይነትን ማስፈን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትሆን ሀገር ለመገንባትና ሁላችንንም የጋራ አሸናፊ ለማድረግ ያግዘናል፡፡
በመሆኑም ሁሉም አካል በምክክሩ በንቃት እንዲሳተፍ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
ምክክር ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረመንግሥት ግንባታ!
ተጨማሪ መረጃ

