በሐረር ከተማ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የሐረሪ ክልል ባህል ማዕከልን የጋዜጠኞችና የኮሙኒኬሸን ባለሙያዎች ቡድን ዛሬ ጎብኝቷል፡፡

|

በሐረር ከተማ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የሐረሪ ክልል ባህል ማዕከልን የጋዜጠኞችና የኮሙኒኬሸን ባለሙያዎች ቡድን ዛሬ ጎብኝቷል፡፡

የባህል ማዕከሉ የወጣቶችን ስብዕና ለመገንባት እንዲሁም ስለ ሃገራቸውና ስለ ሃረሪ ክልል ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች ለማስተዋወቅ ያስችላል ተብሏል። ሐረር የመቻቻልና የፍቅር ከተማ መሆንዋን በተጨባጭ ለማሳየትና የቱሪዝም ማዕከልነቷን ለማሳደግ የባህል ማዕከሉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ተናግረዋል፡፡

የባህል ማዕከሉ የወጣቶች ስብእና መገንቢያ ማዕከላት፣ የቤት ውስጥ መጫወቻዎች፣ የሐረሪ እና የኦሮሞን ባህል የሚያንጸባርቁ ጎጆዎች፣ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል የስብሰባ አዳራሽን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት መስጫዎችን ያካተተ ነው።

የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ቡድኑ የሃረርን ታሪካዊነት በጠበቀ መልኩ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚሰሩትን ስራዎችን እንዲሁም የትምህርትና የመንገድ መሰረተ ልማቶችንም ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።

በትምህርት ዘርፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ 4 በከተማ እና 4 በገጠር ቀበሌዎች የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አብይ አበበ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ተማሪዎች ትምህርት ለማግኘት በአማካይ ከ1.5 ኪሎ ሜትር በላይ እንዳይጓዙ ለማድረግ ክልሉ እየተሰራቸው ያሉ ተግባራት ውጤት እያስገኙ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በመንገድ ልማት ዘርፍ በከተማዋ ከ61 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከተገነባው የአስፋልት መንገድ በተጨማሪ የሐረር ከተማን ከገጠር ቀበሌዎች ጋር እንዲሁም የገጠር ቀበሌዎችን እርስ በእርስ የማስተሳሰር ስራ ትኩረት እንደተሰጠው የክልሉ የትራንስፖርትና መንገድ ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር ጠይባ አብደላ ተናግረዋል።

Similar Posts