በሚዲያና ኮሙኒኬሸን ዘርፍ ተዋናዮች መካከል ያለው ቅንጅት እየተሻሻለ መምጣቱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ።
በርካታ ሃገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በባለፉት ስድስት ወራት ውጤታማ ሥራዎችን ለመስራት መቻሉንም አንስተዋል። ይህንን ለማሳካት ለደከሙ የዘርፉ ተዋንያን በሙሉም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የፌዴራልና የክልል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት የግማሽ አመት የጋራ ጉባኤ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በሰላም አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የተሰራው ስራና አፈፃፀሙ ላይ ከክልልና ከተቋማት የኮሙኒኬሽን ዘርፍ እንዲሁም ከሚዲያ ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
ባለፉት ስድስት ወራት የሃገራችንን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ የተከናወኑትን ተግባራት ውጤታማ ለማድረግ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና ከፍተኛ እንደነበር የተናገሩት የአገልግሎቱ ሚኒስትር በዚህም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ሥራዎች ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ላይ ሲሰነዘሩ የነበሩ ተጽዕኖዎችን በሚዲያና ኮሙኒኬሸን ሥራዎች ለመመከት ሲሰራ መቆየቱን ሚኒስትሩ ጠቁመው በዚህም ሃገራችን ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በስኬት ለማስተናገድ መቻሏን ገልጸዋል፡፡
በኢኮኖሚ ዘርፍ በተለይ የበጋ ስንዴና የአረንጓዴ አሻራ እንዲሁም የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ ሌሎችም ሃገራዊ አጀንዳዎች በተቀናጀ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ስራ እንዲታገዙ ለማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት በመገንባት ሂደት ላይ ያለች ሃገር በመሆንዋ በርካታ ውስብስብ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ መገደዷን ያነሱት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ እነዚህ ፈተናዎች በተለያየ መልኩ የሚገለጹ መሆኑንና ፈተናዎቹን ለመጋፈጥም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ከፍተኛ ሃላፊነት እንደተጣለበት አንስተዋል።
በቀጣይ ዘርፉን እየፈተኑ የሚገኙ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለመለየትና መፍትሄንም ለማስቀመጥ ጉባኤው ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው በማንሳት ኢትዮጵያን የሚመጥን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ ለመስራት ትልቅ የቤት ስራ የተጣለበት ተቋም መሆኑንም በንግግራቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ የክልል የኮሙኒኬሸን ቢሮዎች እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት ይካሄዳል።
በተጨማሪም የፌዴራልና የክልል የኮሙኒኬሸን ግንኙነት ሪፖርትም ለውይይት ይቀርባል።
በግማሽ አመት የጋራ ጉባኤው በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና በክልሎች መካከል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሴክተር የአሰራር መመሪያ የመግባቢያ ሰነድ ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጉባኤው ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሁሉም ክልሎች የኮሙኒኬሸን ቢሮ ሃላፊዎችና ተወካዮች፣ የፌዴራል ተቋማት የኮሙኒኬሽን ሃላፊዎች፣ የሚዲያ አመራሮች እና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡