በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተከትሎ ትልቅ ምጣኔ ሃብታዊ ውጤት እንደሚያስገኙ ከታመነባቸው እርምጃዎች መካከል የነፃ ንግድ ቀጠናዎችን ማስፋፋት ተጠቃሽ ነው።

በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተከትሎ ትልቅ ምጣኔ ሃብታዊ ውጤት እንደሚያስገኙ ከታመነባቸው እርምጃዎች መካከል የነፃ ንግድ ቀጠናዎችን ማስፋፋት ተጠቃሽ ነው።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በመተባበር ያዘጋጁት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጉብኝት መርሃግብር የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠናን በመጎብኘት ዛሬ ተጀምሯል።
ጉብኝቱን የመሩት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) 55 የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራትን አንድ ላይ በማሰባሰብ በተሳታፊ ሃገራት ብዛት በዓለም ትልቁ ነፃ የንግድ ቀጠና እንደሆነ አንስተው የስምምነቱ ዋና ዓላማም የንግድ እንቅፋቶችን በማስወገድ የርስበርስ ንግድን ማሳደግ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ቀጠናዊ የእሴት ሰንሰለትን በመፍጠር በአህጉሪቱ ውስጥ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ንግድ ማበረታታት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ይህም አህጉራዊ የኢንዱስትሪ ልማትን በማጎልበትና የስራ እድልን ለመፍጠር የሚኖረውን አስተዋጽኦ ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ ኢትዮጵያም ስምምነቱን በቀዳሚነት ከፈረሙ ሃገራት መካከል አንዷ ናት። ከስምምነቱ ውስጥ አንዱ ምሰሶ የአፍሪካ ሃገራት የአምራች ዘርፋቸውን ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችንና ነፃ የንግድ ቀጠናዎችን በማስፋፋት እንዲያግዙ እንዲሁም ግልፅ የፓሊሲ አቅጣጫን እንዲከተሉ ማድረግ ነው።
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠናም ይህንኑ አላማ ለማሳካት በማቀድ ተመስርቷል።
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና በተለይ በሎጂስቲክስ ምክንያት በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ ያለውን ማነቆ ለማስወገድ ትልቅ ሚና እንዳለውም የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ረሺድ አስታውቀዋል። አምራች ተቋማቱ ምርቶቻቸውን ለሃገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን እድል መፍጠሩንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ያላት የንግድ ትስስር እያደገ በመምጣቱም ሂደቱን በግልፅ ፖሊሲ ለመደገፍና ተወዳዳሪነቷን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑም በጉብኝቱ ወቅት የተነሳ ጉዳይ ነው።
በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙት የመኪና መገጣጠሚያ፣ የክር ማምረቻ ፋብሪካና የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎቹ ዛሬ ተጎብኝተዋል።