“በኮሙኒኬሽን ተቋማትና የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሮች የሚከናወኑ የተግባቦት ሥራዎች ዓላማ ተኮር እና ብሔራዊ ጥቅሞችን የሚያስገነዝቡ መሆን ይገባቸዋል” – የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

****************************

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሀገራዊ የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች አፈጻጸምን ገምግሟል፡፡ በበይነ መረብ በተካሄደዉ የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ የክልል እና ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ተቋማት እና የፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

የአገልግሎቱ፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ተቋማት እና የፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ክፍሎች የሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸሞች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በሩብ ዓመቱ በተናበበ እና በተቀናጀ የጋራ ዕቅድ በመመራት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና የሕዝብን የመረጃ ፍላጎት የሚያሟሉ መረጃዎች ተደራሽ መደረጋቸው፣ ኹነቶችና የንቅናቄ አጀንዳዎች በተቀናጄ መልዕክትና የሚዲያ ስምሪት መመራታቸው በጥንካሬ ተነሥተዋል፡፡

የመጀመሪያዉ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ጥሩ መናበብ የታየበትና ወጥ ሀገራዊ የኮሙኒኬሽን ሪፖርት ማቅረብ የተጀመረበት እንደነበር ያስታወሱት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) በቀጣይ የበለጠ ቅንጅትና ተናባቢነት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

የተግባቦት ሥራዎች ዓላማ ተኮር እና ሀገራዊ ትልሞችን የሚያስገነዝቡ መሆን እንደሚገባቸው ያሳሰቡት ዶ/ር ለገሠ “በቀጣይ የምንሠራቸዉ የተግባቦት ሥራዎች የመንግሥትን እና የሀገርን ትልሞች የሚያስገነዝቡ፣ የተሳሳቱና ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያርሙ፣ የሕዝብን የመረጃ ፍላጎት የሚመልሱ እና ሁሉንም የሚዲያ አማራጮች የሚጠቀሙ መሆን አለባቸው፡፡ በውጤቱም የሕዝብን እና መንግሥትን ትምምን ማጠናከር፣ የሀገር እና የመንግሥትን ገጽታ መገንባት ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡

በተለይ በሀገር ላይ የሚቃጡ አሉታዊ እና የተቀናጁ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ሀገራዊ ሕልሞችን ለማሳካት ምልዓተ ሕዝቡን የሚያነሣሡ መረጃዎችን በየጊዜዉ በመስጠት የሚዲያ አጀንዳ ብልጫ መውሰድ እንደሚገባ ዶ/ር ለገሠ አሳስበዋል፡፡

የተግባቦት ሥራዉ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርሞችን እንዲሁም ማኅበራዊና ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን በተጨባጭ ማስገንዘብ ላይ ማተኮር እንዳለበትም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የክልል እና የከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች እና የፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች የዘርፉ አደረጃጀት እና መዋቅር እየተጠናከረ የተግባቦት ሥራዉ እንዲጎለብት አገልግሎቱ ድጋፍና ክትትሉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የመንግሥት መረጃ ተደራሽነትን በመምራት፣ የተናበበና የተቀናጀ ተግባቦትን በማጎልበት የሀገርና የመንግሥት ገጽታን የመገንባት ሚናን እንዲወጣ በደንብ ቍጥር 488/2014 መቋቋሙ የሚታወስ ነው፡፡

Similar Posts