በዛሬው እለት በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተደረገውን ሕዝባዊ ትዕይንት አስመልክቶ ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ (የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር) መልዕክት
ዛሬ በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ሕዝባዊ ትዕይንቶች ተደርገዋል። ሕዝቡ በዚህ ትዕይንተ ሕዝብ ላይ ለሰላም ያለውን አቋም በድጋሚ ገልጿል።
ፀረ ሰላምና ተላላኪ ኃይሎች በሚፈጽሙበት ግፍ ተማሯል። በደሙና በላቡ የገነባቸው መሠረተ ልማቶች ‘የአንተ ነን’ በሚሉት የጠላት ተላላኪዎች ሲፈርሱበት በአይኑ አይቷል። ልጆቹ ከትምህርት፣ ከብቶቹ ከግጦሽ እየተከለከሉ እጅ ከወርች ታስሮ ከርሟል።
በዚህ የተነሣ ተላላኪዎቹን ጽንፈኞች ለመታገል ቆርጦ የተነሳው ሕዝብ ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል። በዛሬው ትዕይንተ ሕዝብ መሬቱ እስኪንቀጠቀጥ ወጥቶ ቁጣው ያስገመገመውም ለዚህ ነው።
ሕዝብ ሰላም ፈልጓል። መንግሥትም ሰላም ፈልጓል። ፀረ ሰላምና ተላላኪዎቹ ማን እንደሆኑ ታውቋል። ይሄንን አካል ሕዝብና መንግሥት በአንድ ግንባር ተሰልፈው፤ ገጥመው፣ በግልጽ አደባባይ አሸንፈውታል። ነገ ዛሬ ታይቷል።
ተላላኪን የሚያሠማራው ላኪ ነው። ላኪዎችን ደግሞ መንግሥትም ሕዝቡም ጠንቅቆ ያውቃቸዋል። የላኪዎችን ማንነት ብቻ ሳይሆን ወቅታዊ እንቅስቃሴ እና ያሰከራቸውን የሤራ ፖለቲካም ጭምር ሕዝብ ነቅቶባቸዋል። ላኪም ተላላኪም ከመንግሥትና ከሕዝብ በላይ አለመሆናቸውን ሊገነዘቡት ይገባል።
በአደባባይ ሀቁን ላሳዩት በየደረጃው ያሉ ጀግና የአማራ ክልል አመራሮች እና ለመላው ሰላም ወዳድ ህዝብ ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ።





