“በጂኦ ፖለቲካ ውጥረት እና በኢ-ተገማች ዲፕሎማሲ በሚስተዋልበት ሁኔታ በሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ችለናል” አቶ አደም ፋራህ
በጂኦ ፖለቲካዊ ውጥረት፣ በኢ-ተገማች የታሪፍ ዲፕሎማሲ፣ በአቅርቦት ሠንሰለት መቆራረጥ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ፣ የተዳከመ የማክሮ ኢክኖሚ ዓውድ በሚስተዋልበት ሁኔታ፣ በሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስቀጠል መቻሉን በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ኃላፊ ክቡር አቶ አደም ፍራህ ገለጹ።
ለዚህ አመርቂ ውጤት መመዝገብ ያበቃን የሦስት ዋና ጉዳዮች ድምር ውጤት ነው ያሉት አቶ አደም ፋራህ፣ እነዚህም ከለውጡ ወዲህ የዕይታ ለውጥ መምጣት መቻሉ፣ የአመራር የማስፈጸም ዐቅም ትጋትና ቁርጠኝነት እንዲሁም የሕዝቡ እና የግል ሴክተሩ ተሳትፎና ትብብር እንደሆነም ገልጸዋል።
አቶ አደም ፋራህ አክለውም በመደመር እሳቤ ሁሉንም አቅጣጫዎች ደምረን እንጠቀም ያሉ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ዘርፍ ለሀገር ዕድገት እና ብልጽግና ማበርከት የሚገባውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የብዝሀነትን አቅጣጫ እንከተል ሲሉም ተናግረዋል።
በመፍጠን እና በመፍጠር መርህ በትጋት መሥራት ይኖርብናል ያሉት አቶ አደም ፋራህ ፈተናዎችን ወደ ድል እየቀየርን፣ ሳንሸነፍ ያቀድናቸውን በስኬት ተግባራዊ ለማድረግ እንቀሳቀሥ፣ የሚል እሳቤ ተይዞ በመሠራቱ የተገኘ ውጤት እንደሆነም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 ዓ.ም የመጀመርያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ግምገማ በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

