ቱሪዝም የኢኮኖሚ እድገቱን ዘላቂነት እያጎለበተ ነዉ
ታህሳስ 16/2018 ዓ.ም
የቱሪዝም ዘርፍ ከሀገራዊ የልማት አጀንዳ ውስጥ አንዱ የስትራቴጂክ ምሰሶ በመሆኑ መንግሥት የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል፣ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር እና የአገሪቱን ዓለም አቀፋዊ ገጽታን ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፣ አመርቂ ዉጤቶችም ተመዝግቧል፡፡
በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሃገር እና ገበታ ለትውልድ የተሰሩ ፕሮጀክቶች ማለትም የወንጪ ደንዲ፣ ጎርጎራና ሀላላ ኬላ ኢኮ-ቱሪዝም፣ እንዲሁም በብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ ኢኮ-ሎጆች የአካባቢ፣ የባህል ጥበቃን እና የማህበረሰብ ተሳትፎን ያጣመረ አዲስ የዘርፉ እሳቤ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ ይህም በተፈጥሮ ማራኪ የሆኑ ስፍራዎችን ወደ ሀብትነት በመቀየርና የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን በመሳብ ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ እንዲነቃቃ ማድረግ ተችሏል፡፡
የቱሪዝም ዘርፍ የሀገሪቱን የበለፀጉ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና የተፈጥሮ ሀብቶችን በመጠቀም፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ዋና ምንጭ እና ሁሉን አቀፍ እድገት አንቀሳቃሽም እየሆነም መጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን ቅርሶች በማደስ ፣ በመጠበቅ በዩኔስኮ እንዲመዘገቡና ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ በማድረግ፣ የቱሪስት መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ ሰፊ ስራ ተሰርቷል።
ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት የኢትዮጵያን ገጽታን ከማስተዋወቅና ቱሪዝምን ከማነቃቃት ባሻገር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን እያጠናከሩ ነው፡፡ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ለጋራ ትርክት ግንባታና ብሔራዊ ገፅታን የማስረፅ ከፍተኛ ድርሻ አለው።
አዲስ አበባን የቱሪዝም መዳረሻ፣ የኮንቬንሽን እና ኤግዚቢሽን ማዕከል ለማድረግ ሰፊ ስራ ተሰርቷል። በዚህም የከተማ ማስዋቢያ ፕሮጀክቶችና መሠረተ ልማትን በማስፋፋት፣ የእንግዳ ተቀባይነትን በማሻሻል እና የባህልና ኮንፈረንስ ቱሪዝምን በማስተዋወቅ አዲስ አበባን ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በልዩ ትኩረት በተሰራ ስራ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማስተናገድ ተመራጭ እየሆነች ነው።
አሁን ላይ የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት በመላዉ ሀገሪቱ የሚገኙ አዳዲስ የቱሪዝም መስህቦችን ማልማትና ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማደስ ሲሆን፣ በዚህም ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተከናዉነዋል፡፡ እነዚህ የቱሪዝም መዳረሻዎች ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ለመሳብ ብቻ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን እና ሁሉን አቀፍ ልማትን ለመደገፍ የታለሙ ናቸው፡፡
መንግስት በዘርፉ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጉ ሌላኛዉ ወሳኝ ስኬት ሲሆን፣ የተቋማዊ ቅንጅት እንዲጠናከር ከማድረጉም ባሻገር ቱሪዝምን ከመሠረተ ልማት መስፋፋት፣ ዲጂታል ሽግግርን እና የስራ ፈጠራን ጨምሮ ጠንካራ የሆነ ሀገራዊ ስትራቴጂ እንዲዘጋጅ አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለ ሀብቶች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
በአጠቃላይ የሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ራዕይ አካታችነትን ማሳደግ፣ የአካባቢ ማህበረሰቦችን በማሳተፍ እና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎን በማበረታታት እና የኢኮኖሚ እድገቱን በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነዉ፡፡
ለተጨማሪ መረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

