ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም ከውስጥና ከውጪ በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሟትም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቧን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በአዳማ የፌዴራል እና የክልል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዓመታዊ የጋራ መድረክን ሲከፍቱ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ 5ኛ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ደረጃ ላይ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

በሃገሪቱ የተመዘገቡት ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ሁሉም ጠንካራ የሚዲያና እና የኮሙኒኬሽን ተግባቦት ሥራ ድጋፍ እንደነበራቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ ስኬቶቹ ግን በርካታ ፈተናዎችም እንደነበሩባቸው ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ጽንፈኝነትና አክራሪነት እንደ ሃገር ሲፈትኑን እንደነበር የጠቆሙት ሚኒስትሩ በተለይ በትክክለኛ መረጃ ላይ ከመመስረት ይልቅ በሀሰት በሚነዙ አሉባልታዎች አንዱን አካባቢ ከሌላው ጋር ለማጋጨት ሲፈጸሙ የነበሩት የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች ትልቅ ፈተና እንደነበሩ አንስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ በሁሉም አከባቢዎች የሰፈነውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም በግብርናው ዘርፍ በበጋ መስኖ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በማእድን፣ በቱሪዝም ዘርፎች የተጀመሩት ሥራዎች ውጤታማ እንደሆኑ አንስተዋል፡፡ በቀጣይ 2ኛው ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድ ተግባራዊ የሚደረግበት በመሆኑ ሁሉም አካላት በመናበብ ሊሰሩ እንደሚገባ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በሁሉም የመንግስት መዋቅር ውስጥ የተቀናጀ፣ የተናበበ እና ውጤታማ የተግባቦት ስርአትን መዘርጋት በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት የሚከናወን ተግባር መሆኑን የገለጹት ዶክተር ለገሰ በተለይ በትምህርት ዘርፍ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚከናወኑ ሥራዎች እና በጤናው ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች ሰፊ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሽፋን ሊሰጣቸው እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በአዳማ የሚካሄደው ዓመታዊ ጉባኤ የሐረሪ፣ የደቡብ ምዕራብ ክልሎች የኮሙኒኬሽን የሥራ አፈጻጸም እንዲሁም ከፌዴራል ተቋማት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ስራዎች አፈፀፀም ይቀርባል። በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኩል በክልሎችና በተቋማት የኮሙኒኬሽን መዋቅር የተደረገው ምልከታ ውጤት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃል፡፡

Similar Posts