ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ወራት 250ሺህ ቶን የማር ምርት አግኝታለች

ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ወራት 250ሺህ ቶን የማር ምርት ማግኘቷን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ አመላከተ፡፡
በግብርናዉ ዘርፍ በተለይም የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ተቀርጾ እየተተገበረ ያለዉ ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ከፍተኛ ዉጤት ማስመዝገቡን ቀጥሏል፡፡
በምግብ ራስን ለመቻል መንግስት በሌማት ትሩፋት እና በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየከናወነ ያለው የግብርና እና የአከባቢ ጥበቃ ልማት ሥራ ንብ ለማነብ እና የማር ምርታማነትን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። በዚህም የማር አመራረትን ለማዘመን በተሰጠው ትኩረት ባለፉት አሥር ወራት እንደ ሀገር 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዘመናዊ ቀፎ መሰራጨቱንና 250ሺህ ቶን የማር ምርት መግኘቱ ተጠቅሷል፡፡
የወቅቱ የዝናብ ስርጭት ምቹ መሆን፣ የደኖች መስፋፋት እና በመስኖ ልማቱ ንቦች የሚቀስሟቸው የአበባ ዛፎች በስፋት መኖር ለተገኘዉ ከፍተኛ የማር ምርት ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ይህ ውጤት የዉጭ ምንዛሪ ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ ሚና የሚኖረው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ከ2.2 ሚሊዮን በላይ ንብ አናቢዎች እና ከ12 ሚሊዮን በላይ ህብረ ንቦች የሚኖሩ ሲሆን፣ ይህ ሀገሪቱ በንብ መንጋ ብዛትና በማር ምርት ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን የሚያሳይ ነዉ፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷና በተፈጥሮ በታደለችው የአየር ጸባይ ለማር ምርት ምቹ በመሆኗ፣ ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን አርሶ አደሩ በትኩረት መስራት እንዳለበት ይጠበቃል፡፡