ኢትዮጵያ ከንኡስ ነጠላ ትርክት ወደ ታላቅ ሕብረ ብሄራዊ ገዥ ትርክት መሻገር ይጠበቅባታል ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንቱ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክርቤቶች 4ኛ የሥራ ዘመን የጋራ ጉባኤ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ገዥ ትርክትና አሰባሳቢ ትርክትን ያጸኑ ሀገራት ዛሬ ስፍራቸው ታላቅነትና ብልጽግና ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወርዷን በሚመጥን ልክ ከሕዝቦችዋ አልፋ በዓለም አምራና ደምቃ መታየት ይኖርባታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ለሁላችንም አታንስም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ በበጀት ዓመቱ መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ አፈጻጸም የሚያሻሽልበት እንደሆነ ጠቁመው መንግስት በተናጠልም ይሁን በጋራ በሰላም ጉዳይ ለመነጋገር በሮቹ አሁንም ወለል ብለው የተከፈቱና ለመነጋገር ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከሰላማዊ መንገድ ውጭ የሀይል አማራጭን በመጠቀም የፖለቲካ ፍላጎትን ለማስፈጸም የሚደረጉ ማናቸውም ዕኩይ ተግባራት መንግስት በልበ ሰፊነት የሚያሳልፍበት ዕድል የጠበበ ነው ብለዋል፡፡

በልበ በሰፊነት በቂ ጊዜ ተሰጥቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ የሕዝቦችን አብሮነት፣እሴት የሚያላሉ ፣በጥላቻ ንግግር የሕዝብን አብሮነት አደጋ ላይ የሚጥሉና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰዳል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

Similar Posts