ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን እንድታስተናግድ መመረጧ በወሳኝ የወቅቱ ጉዳዮች ላይ የዓለማቀፍ ትብብር እና ውይይት ማእከል መኾኗን የሚያመለክት ነው” የአፍሪካ ኅብረት

ኅዳር 06/2018 ዓ.ም

የአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያ 32ኛውን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚመክር እና ኮፕ በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ጉባኤ እንድታስተናግድ በመመረጧ የተሰማውን ደስታ ገለጸ፡፡

የኅብረቱ ኮሚሽነር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ለኢፌዴሪ መንግሥት ባስተላለፉት የእንኳን ደስ ያለን መልእክት “እንደ አፍሪካ ኅብረት መዲናነቷ እና የበርካታ ዓለማቀፋዊ እና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ማእከልነቷ አዲስ አበባ 32ኛዉን የኮፕ ጉባኤ እንድታስተናግድ በመመረጧ ደስታ ተሰምቶናል” ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው አመራር በዘላቂ ልማት እና አካባቢ ጥበቃ ረገድ እያሳያ ያለው ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት የአፍሪካን በዘርፉ ላይ ያለ ቁርጠኝን አመላካች ተደርጎ እንደሚወሰድም ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ በርካታ አፍሪካውያንን እያነሣሣ ያለ ተግባር መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን እንድታስተናግድ መመረጧ በወሳኝ የወቅቱ ጉዳዮች ላይ የዓለማቀፍ ትብብር እና ውይይት ማእከል መኾኗን የሚያመለክት ነው” ሲሉም የኅብረቱ ኮሚሽነር አሊ ዩሱፍ አስገንዝበዋል፡፡

“ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ አህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ ትልልቅ ኹነቶችን በስኬት የማስተናገድ ልምድ አላት፤ የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ጨምሮ በርካቶችን በስኬት አስተናግዳለችና” ያሉት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ኮፕ-32ን እንድታስተናግድ መመረጧ ለአፍሪካ ኩራት መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ኅብረቱ በጉባኤዉ ዙሪያም ከኢትዮጵያ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2027 (እ.አ.አ) የሚካሄደዉንና 32ኛዉን የኮፕ ጉባኤ እንድታስተናግድ የተመረጠችው የ31ኛዉን ጉባኤ አስተናጋጅ ለመለየት ተወዳዳሪ አገራት ገና እየተፎካሩ ባሉበት የብራዚሏ ቤለም ከተማ በስተናገደችው ኮፕ-30 መድረክ ነው፡፡ በ30ኛዉ መድረክ ከ50 ሺህ በላይ ከተለያዩ አህጉራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ከዓመት በፊት አዘርባጃን ባስተናገደችው 29ኛዉ ጉባኤ ከ72 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ነበሩ፤ በአዲስ አበባዉ መድረክ ከእነዚህም ቁጥሮች የላቀ ተሳታፊ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡

Similar Posts