“ኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ሽግግርን እዉን ለማድረግ ስኬታማ ስራዎችን አከናዉናለች” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለዉ 2ኛው የተባበሩት መንግስታት የምግብ ስርዓት ጉባኤ (UNFSS+4) ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ሽግግርን እዉን ለማድረግ ስኬታማ ስራዎችን ስታከናዉን መቆየቷን ገልጸዋል፡፡ በመላው አፍሪካ የምግብ ሥርዓትን ለመለወጥ እየተሰሩ ያሉ አኩሪ ስራዎችንም አድንቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዓለም አቀፍ መሪዎች፣ የልማት አጋሮች እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተገኙበት ባደረጉት ንግግር፣ ረሃብን፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን እና የአየር ንብረት ተጋላጭነትን ለመከላከል ዘላቂ፣ ሁሉን አቀፍ እና የማይበገር የምግብ ስርዓት መገንባት ጊዜ የማይሰጠዉ አንግብጋቢ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችውን የአየር ንብረት ለዉጥ መከላከያ ስትራቴጂ፣ የተቀናጀ የግብርና ፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ እንዲሁም ለአመጋገብና ፍትሃዊነት ቅድሚያ የሚሰጡ የማህበረሰብ አቀፍ መፍትሄዎችን ለጉባኤዉ አብራርተዋል።

“የምግብ ስርዓት ግብርና ብቻ ሳይሆን የሀገር ክብር፣ ሉዓላዊነት እና የህልውና ጉዳዮች  ናቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የረዥም ጊዜ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በአፍሪካ የሚመራ ፈጠራ እና ኢንቨስትመንት ስራዎች መስፋፋት አለባቸዉ ብለዋል፡፡

በተለይም የአፍሪካ ሀገራት በምግብ ራሳቸዉን እንዲችሉ ጉባኤው በትብብር እያደረገ ያለዉን ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን በአጽኖት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትረ በቀጣይ አጋር አካላት  የአፍሪካን ልዩ ተግዳሮቶች እና እድሎች የሚያንፀባርቁ በአገር ውስጥ የተዘጋጁ መፍትሄዎችን እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከሐምሌ 21-22/2017 እየተካሄደ ያለዉ 2ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባኤ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና ሞሀመድና ሌሎች የሀገራት መሪዎች የተገኙ ሲሆን፣  ከ2021 ጉባኤ ወዲህ ያለውን ሂደት ለመገምገም እና የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን  ለማፋጠን ያስችላል፡፡

Similar Posts