ወቅታዊ መረጃ

በአፋር፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ማከዕሉን ያደረገ የተለያየ መጠን ያለው የርዕደ መሬት በተደጋጋሚ መከሰቱ ይታወቃል።

ክስተቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠን እየጨመረ ይገኛል። በተለይም በዚህ ሳምንት በርዕደ መሬት መለኪያ እስከ 5.8 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ መንቀጥቀጥ መከሠቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

መንግሥት ክሥተቶተቱን በቅርበት እየተከታተለ ይገኛል። በተለይ የርዕደ መሬቱ ማዕከል (epicenter) የሆኑት አካባቢዎችን በመለየት በ12 ቀበሌዎች ላይ መንግሥት ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በቦታው በማሰማራት የጉዳቱን መጠን አሠሣ እያደረገ ይገኛል። በእነዚህ ቀበሌዎች ከሚኖሩ 80ሺህ ዜጎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማራቅ ለማሥፈር ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው።
በተጨማሪም ርዕደቱ በማኅበራዊ አግልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ በኢኮኖሚ ተቋማት እና በመሠረተ ልማት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽዕኖ በመከታተል ላይ ነው።
እስካሁን ባለው ሁኔታ በዋና ዋና ከተሞች የጎላ ተጽዕኖ ያላደረሰ ቢሆንም ዜጎች በባለሞያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ መልእክቶችን እንዲከታተሉና በጥብቅ እንዲተገብሩ ለማሳሰብ እንወዳለን።

በቀጣይም ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል አስፈላጊ መረጃዎችን በሚመለከታቸው ተቋማት አማካይነት የሚያደርስ መሆኑን መንግሥት ያስታውቃል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣
ታኅሣሥ 26 ቀን 2017

Similar Posts