የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ የለም ብለዋል።

|

ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ በመግለጫቸው ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል ተከታዩቹ ይገኙበታል።

ማሻሻያው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ የሁለተኛው መካከለኛ ዘመን መርሃ ግብር ምሰሶ የሆኑ አራቱን መሰረታዊ ጉዳዮች ማለትም፦

1) በሀገሪቱ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታን መፍጠር

2) የንግድ ስራዎችን የሚያሳልጡ የሚያቃልሉና ውጤታማነትን የሚያሻሽሉ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን ማሻሻል

3) የዘርፎቹች ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን የማሳደግ እና የመንግስት የማስፈጸም አቅምን ማጎልበትን

4) ማሻሻያዎቹ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን መቀነስና የንግድ ዕድሎችን በማስፋት የግል ሴክተሩ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ጉልህ ሚና የሚያሳድጉ ናቸው፡፡

የፋይናንስ እና መወቅራዊ ማሻሻያ እርምጃዎቹ ይበልጥ አሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ጠንካራ እና ዘላቂ ወደሆነው የኢኮኖሚ አቅም ለመሸጋገር ሀገሪቷ የምታደርገዉ ጥረት አካል ናቸው፡፡

* አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡

ለዚህ ሶስት መሠረታዊ ምክንያቶች አሉ፡፡

1) በአሁኑ ወቅት በገበያው ላይ ያለ ከውጪ የገባዉ ሸቀጥ ከማዳበሪያ፣ ነዳጅ እና ብድር በቀር በፍራንኮ ቫሉታ የገቡትን ጨምሮ አብዛኞቹ በጥቁር ገበያ የምንዛሪ ተመን ተገዝተው የገቡና ከዚህ ቀደም የዋጋ ማስተካካያ የተደረገባቸዉ ናቸው፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ መሰረት ገበያ በወሰነው የዶላር ምንዛሪ ተመን ሸቀጦችን ገዝቶ ወደ አገር ቤት ለማስገባት ቢያንስ ወራት ይፈጃል። ስለሆነም እየተደረገ ያለው የዋጋ ጭማሪ ምንም ዓይነት ምክንያታዊ መሠረት የለውም ማለት ነው፡፡

2) መንግስት የወሰደው የማሻሻያ እርምጃ ሁለት የተራራቁ ገበያዎችን የማቀራረብ ወይም ኢመደበኛ የሆነውን የኢኮኖሚ ስርዓት ወደ መደበኛ የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲቀየር ያደረገ ነው፡፡ በቀላል አነጋገር ህገ ወጥ የነበረውን አካሄድ ወደ ህጋዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነው የቀየረው፡፡ ስለሆነም በተለያዩ ችግሮች ወደ ህገወጥነት የገቡ ኃይሎች በህጋዊ መንገድ የሚፈልጉትን ነገር እንዲያገኙ ሁኔታዉ እየተመቻለቸዉ ወደ ሌላ ህገ ወጥ ተግባር እንዲገቡ የሚያስገድድ ምንም ምክንያት የለም፡፡

3) የተደረገዉ ማሻሻያ የንግዱ ማህበረሰብ ራሱ ሲጠይቀው የኖረው ጥያቄ ነው፡፡ በመሆኑም ራሱ ለጠየቀዉ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ሲሰጥ ህገወጥነትን ማበረታታት ተቀባይነት እንደሌለዉ በመገንዘብ ወደ ህጋዊና መደበኛ የኢኮኖሚ ስርዓት መግባት አለበት፡፡

ስለሆነም መንግስት በንግድ ስርአቱ ውስጥ አላግባብ የምርት እጥረትና ዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላት ላይ የጀመረዉን ህግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

Similar Posts