የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የክልል የኮሙኒኬሽን ተቋማት ያሉበትን ደረጃ ለማወቅና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በዘጠኝ ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ሲያካሂድ የቆየውን የክትትልና ድጋፍ ሥራ አጠናቋል

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የክልል የኮሙኒኬሽን ተቋማት ያሉበትን ደረጃ ለማወቅና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በዘጠኝ ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ሲያካሂድ የቆየውን የክትትልና ድጋፍ ሥራ አጠናቋል፡፡

አገልግሎቱ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል የተቀናጀ እና የተናበበ የተግባቦት ሥራ ከፌዴራል እና ከክልል ኮሙኒኬሽን ተቋማት ጋር መዘርጋት፣ በትብብር መሥራት እና ለክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮዎች የተግባቦት ሥራን ለማከናወን የሚያስችል አቅም መገንባት ይገኝበታል፡፡

ይህንን ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የኮሙኒኬሽን መዋቅሮች ያሉበትን የስራ ሁኔታ ማወቅ ቀዳሚ ተግባር ነው። በዚህም ከግንቦት 28 ጀምሮ በዘጠኝ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

የክትትልና ድጋፍ ሥራዎቹ በዋናነት ክልሎቹ እና ከተማ አስተዳደሮቹ በኮሙኒኬሽን ዘርፍ ያላቸው አደረጃጀትና የሰው ኃይል፣ ከእቅድ ዝግጅት አንጻር ያሉበት ደረጃ፣ የግንኙነት አግባብ፣ ከፌዴራል ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና ከክልሎች ከዞንና ከወረዳዎች ጋር ያሉ ትስስሮች፣ የሚዲያ አጠቃቀም፣ የይዘት ዝግጅት፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የመረጃ አያያዝና ሥርጭት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ በሁሉም ቢሮዎች የተካሄደው ምልከታ ለኮሙኒኬሽን መዋቅሩ የሚያስፈልጉ የድጋፍ ማዕቀፎችን ለመዘርጋት የሚያግዙ ግብአቶችን ለማሰባሰብ ያስቻለ ነው።

በቀጣይ የክትትልና ድጋፍ ቡድኑ ያገኛቸውን መልካም ተሞክሮዎችና ሊስተካከሉ የሚገባቸው አሰራሮች ከክልሎቹ እና ከከተማ አስተዳደሮቹ የኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በሚኖር የጋራ መድረክ ቀርበው ምክክር ይደረግባቸዋል።

Similar Posts