የቢሾፍቱ አየር መንገድ የዲዛይን ሥራው ተጠናቋል – ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የቢሾፍቱ ኤርፖርት የዲዛይን ሥራው ተጠናቋል ሲሉ ጠቅላይ ሚስንትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከዚህ ቀደም አርሶ አደሮች መሬታቸውን ሲለቁ የሚስተናገዱበት መንገድ ስህተት ነበረበት ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ለመቅረፍ ፕሮጀክቱ ሳይጀመር ሙሉ በሙሉ አርሶ አደሮች ደስተኛ ሆነው፣ ኑሮአቸው ተሻሽሎ ከወጡ፣ በአካባቢው የምንገነባው አየር መንገድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያመጣል ብለዋል።
ቢሾፍቱ አየር መንገድ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፉ እንደሚሆን ይጠበቃል ያሉት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በቀጣይነት በአየር ትራንስፖርት ውስጥ ምሳሌ ሆና አፍሪካን ከተቀረው አህጉር ጋር ለማገናኘት ያላትን መሻት ለማሳካት በእጅጉ ያግዛል ሲሉም ተናግረዋል።
በቦሌ አየር መንገድ ከለውጥ በኋላ በርካታ የማስፍፊያ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉ ሲሆን ከ20 ሚሊዮን በላይ ተጓዦችን እንደሚያስተናግድም አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም አዲሱ አየር መንገድ በከፍተኛ ደረጃ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያግዝ፣ ኢትዮጵያን ከዓለም ጋር የሚያገናኝ፣ ለአፍሪካ ጥሩ ብስራት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ያሉ ሲሆን ከ100 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚገመት ኢንቨስትመንት የሚከናወንበት እንደሆነም አብራርተዋል።
የቢሾፍቱ አየር መንገድ ሲጠናቀቅ በዓመት ከ100 ሚሊዮን በላይ ተጓዦችን ያስተናግዳል።

