የኢትየጵያ ጉዞ አፍሪካ ባላት ፀጋና የመልማት አቅም ልክ ለሌላው አለም ልትገለፅ እንደምትችል ማሳያ ነው!! – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ

***************************

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና የሩሲያው አርቲ በጋራ በሚሠሩባቸዉ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ምክክር አድርገዋል፡፡ የአርቲ ዋና ዳይሬክተር እና ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎችን በጽሕፈት ቤታቸዉ ተቀብለው ያነገጋሩት የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ወ/ሮ እናትዓለም መለሰ የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካን ድምፅ አጉልተዉ ከሚያሰሙ እና ሚዛናዊና ትክክለኛ የአህጉሪቱን ትርክት ከሚያንፀባርቁ የሚዲያ ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መነገር የሚገባቸው በርካታ ትልሞች እና ስኬቶች እንዳሏት ያስገነዘቡት ሚኒስትሯ አፍሪካ ባላት ጸጋ እና የመልማት ዐቅም ልክ ለሌላዉ ዓለም እንድትገለጽ ኢትዮጵያ የጀመረችው ጉዞ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል አመላክተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ታሪካዊ እና የረዥም ጊዜ ግንኙነት ካላት ሩሲያ የመጣው አርቲ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ለመሥራት መፈለጉንም አመስግነዋል፡፡

የአርቲ ዋና ዳይሬክተር ቬራ ክሃሪና በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማቲክ ማእከል እና ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ትስስር ያላት በመኾኑ ሚዲያቸው አብሮ የመሥራት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ አርቲ አፍሪካን በተመለከተ የቆየዉን የተዛባ ትርክት ለመቀየር በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

አርቲ የአፍሪካ የሚዲያ ዕውቅና መርሐ ግብር ነገ በአዲስ አበባ ያካሂዳል፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና በመኾኗ ለኹነቱ እንደተመረጠች እና የአፍሪካን የሚዲያ ዐቅም ለማላቅ የተዘጋጀዉ የዕውቅና መርሐ ግብር ነው፡፡

Similar Posts