የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለመገንባትና በዋና ዋና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠር የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች የተናበቡ ሊሆኑ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለመገንባትና በዋና ዋና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠር የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች የተናበቡ ሊሆኑ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ከበደ ደሲሳ ለሁለት ቀናት በአዳማ ሲካሄድ የነበረው የፌዴራል እና የክልል ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዓመታዊ የጋራ መድረክ ማጠቃለያ ላይ እንደተናሩት የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ሥራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ በቅንጅት፣ በመናነብና በመደማመጥ ሙያዊ ስነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ ሊሰሩ ይገባል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት በፌዴራልና በክልል ያሉ የኮሙኒኬሽን ተቋማት አደረጃጀቶችና የአሰራር ችግሮችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ የተገሩት ሚኒስትር ዲኤታው፤ ባለሙያውም የመዋቅርና አሰራር ጉድለቶች እንኳን ቢኖሩ ለሕብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ በመስጠት ሃገራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በቀጣይ ሊከናወኑ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የተናገሩት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው በቀጣይ ሁሉም የፌዴራል እና የክልል ኮሙኒኬሽን መዋቅሮች በሁነት ካላንደር ሥራዎቻቸውን ሊመሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኮሙኒኬሽን መዋቅሮች ስትራቴጂክ እቅድ ከፌዴራል እቅድ እና ከሃገሪቱ የአስር ዓመት እቅድ ጋር መናበብ እንዳለበት ሚኒስትር ዴኤታዋ አንስተው የፌዴራል ተቋማት ከተጠሪ ተቋማት፣ ከክልሎች፣ ከዞንና ወረዳዎች ጋር የተናበበ እቅድ እና የሪፖርት ስርአት ሊኖራቸው ይገባልም ብለዋል፡፡
በክልሎች እንዲሁም በፌዴራል ተቋማት መካከል የልምድ ልውውጦች እንደሚኖሩ ሚኒስትር ዲኤታዋ ጠቅሰው የኮሙኒኬሽን አመራጮች በርካታ በመሆናቸው ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም በተለይም ተቋማዊ የኮሙኒኬሽን ተግባቦትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
ሁለተኛው ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድ ትግበራ በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ ሊታገዝ እንዲገባም በመድረኩ ተነስቷል፡፡
ለሁለት ቀናት የተካሄደው የጋራ ጉባኤ የአገልግሎቱን የ2015 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንዲሁም የፌዴራል እና የክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሥራዎች በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ በመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫን በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡
