የኮሙኒኬሽን ሥራዎቻችን የበላይነትን ይዘው እንዲቆዩ የመንግስትን ዋና ዋና አጀንዳዎች በሚገባ መለየትና በእቅድ አካቶ መስራት እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ፡

የኮሙኒኬሽን ሥራዎቻችን የበላይነትን ይዘው እንዲቆዩ የመንግስትን ዋና ዋና አጀንዳዎች በሚገባ መለየትና በእቅድ አካቶ መስራት እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ በአዳማ እየተካሄደ በሚገኘው “ውጤታማ ተግባቦት ለኢትዮጵያ ልዕልና” የስልጠና መርሃ ግብር ላይ “የሕዝብ ግንኙነትና መሰረቶች፣ አጀንዳ ቀረጻና የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን” በሚል ርዕስ የስልጠና ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደረጎበታል።
ከሃገራዊ አበይት እቅዶች ጋር በማጣጣም የኮሙኒኬሽን አጀንዳን በጥናት ላይ ተመስርቶ መምረጥ፣ ፈተናዎቹን መለየት እንዲሁም በአጀንዳው ላይ የሚሳተፉ አካላትን ማንነትና ድርሻቸውን ማመላከት ከዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ የፖለቲካ አጀንዳ ባለቤት መንግስት እንደመሆኑ ይህንን ለውጤት ለማብቃት በተሟላ ግንዛቤ የመሪነት ሚናን መጫወት፤ እያንዳንዱን የኮሙኒኬሽን ስራም ከትልልቆቹ ሃገራዊ አጀንዳዎች ጋር ማስተሳሰር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የመንግስት አጀንዳዎች የበላይ እንዳይሆኑ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሟቸው አንስተው በተለይ የታቀዱ አፍራሽ አጀንዳዎችን በተቀናጀ መልኩ ለመመከት በየክልሉና በተቋማት የሚገኙ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በእቅድ፤ በተግባርና በመልዕክት መናበብ ይገባቸዋል ብለዋል። የኮሙኒኬሸን ሥራ በስትራቴጂካዊ የኮሙኒኬሽን ዕቅድ ሊመራና የዘርፉ ባለሙያዎች ከሚዲያ ጋር መልካም ግንኙነትን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ዶክተር ለገሰ በገለፃቸው አብራርተዋል።
ለክልልና ለተቋማት የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሃላፊዎችና ለሚዲያ አመራሮች እየተሰጠ በሚገኘው ስልጠና የሚዲያ አመራርና ለህዝብ የሚቀርቡ ንግግሮች እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ያተኮሩ የስልጠና ሰነዶች ለኮሙኒኬሽን ባለሙያዎቹ ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።