የዲጂታል ስትራቴጂ አካታች ለሆነ የኢትዮጵያ ብልፅግና!

ዓለም በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ተጠቃሚነታችንን ለማረጋገጥ እና ወጣቱ በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ስኬታማ እንዲሆን በንቃት መሥራት ይጠበቅብናል። በአሁኑ ወቅት እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence)፣ ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ፣ ናኖ ቴክኖሎጂ እና ቢግ ዳታ ባሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚደገፉ የማምረት፣ የመገናኛ እና የአኗኗር ዘዬ ሽግግርን እየተመለከትን ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ዲጂታል ከባቢ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበለጸገ ህብረተሰብን ለመገንባት የሚያስችላትን አቅም ገና አልፈጠረችም። ዐቅምን በማጠናከር ስኬታማ ለመሆን ደግሞ ፈጣን እና የተቀናጀ እርምጃ ያስፈልጋል። እንደ እኛ በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ ላላቸው ሀገራት የሳይበር ደኅንነት፣ ጎጂ የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት፣ በባለጸጎች እና አነስተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች መካከል እያደገ የመጣው ልዩነት እንዲሁም የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በብቃት መጠቀም ያለመቻል ተጠቃሽ ስጋቶች ናቸው።
አዳዲስ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ዕድገትን ዘላቂ ለማድረግ እና እያንዳንዱ ዜጋ ከሀገር አቀፍ ብልጽግና ተጠቃሚ መሆኑን ለማረጋገጥ ዕድል ይሰጣሉ። እነዚህን የዲጂታል ከባቢ ዕድሎች አሟጦ ለመጠቀም የመንግሥትን አዲስ የmindset እና የአመራር ዘይቤ ይጠይቃል። መንግሥት ለውጪ ግዢና በየጊዜው እያደጉ ለመጡ ቴክኖሎጂዎች መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ እንዲሁም ልዩ ፈጠራ ላላቸውና ቁርጠኛ ለሆኑ ግለሰቦች አዳዲስ ቢዝነሶችንና አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ፣ ሥራዎችን እንዲፈጥሩ የሚረዳ አስቻይ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡
አዳዲስ ዕድሎችን ሙሉ በሙሉ ተገንዝቦ ለመጠቀም በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ ከሚኖሩት መማርን፣ ትብብርን እና አጋርነትን ይጠይቃል ። ይህ ስትራቴጂ የበለጸገው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ መሪዎች ጋር በተደረገ ከፍተኛ ትብብር ነው። በተለይም በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፣ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ Pathway Of Prosperity ኮሚሽን፣ በ Mastercard Foundation ፣ በቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት፣ በ Dal-berg እና በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የጋራ ጥረት ነው። ይህ ስትራቴጂ የመጀመሪያው እርምጃ እና በመሠረታዊነት ወደ ድርጊት የሚያመራ ጥሪ ነው። ለኢትዮጵያ የብልጽግና ተስፋ መሳካት ቃል የገቡ ሁሉ በመተጋገዝ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እንዲያበረክቱ ጥሪዬን አቀርባላሁ። አብረን እንደምናሳካውም ሙሉ እምነት አለኝ ።