“የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ እና የአጠቃላይ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ጥረት አካል ነው።”

የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል “ፅዱ ኢትዮጵያ” በሚል መጠሪያ ሁለተኛዉ ሀገራዊ ንቅናቄ ዛሬ ተጀምሯል። ንቅናቄዉ በአካባቢ ጥበቃ ጽዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን በመፍጠር ለመጪው ትውልድ ኹለንተናዊ ምቹ ሀገር የማስረከቡ ጥረት አካል ነው።

ጽዱ እና ምቹ ኢትዮጵያን ለትውልድ የማስረከብ ጉዞዉ የሚሳካው በየደረጃው ያሉ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን አካላት ጉዳዩን በጥልቀት ተገንዝበዉ ለማኅበረሰብ በማስረዳት እና ሥራዎችን በባለቤትነት ሲመሩ መኾኑ ተገልጿል። የንቅናቄው ማስጀመሪያ አካል የሆነው የሚዲያ አካላት ሚናን የሚመለከት የፓናል ውይይት ግንቦተ 28 ቀን 2017 ዓ/ም በስካይላይት ሆቴል ተካሂዷል።

በፓናል ውይይቱ የተሳተፉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ “የአካባቢ ጥበቃ ከሀገርም አልፎ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ስለኾነ በአጀንዳ የተመራ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ እንደሚያስፈልግ” ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ባለፉት ሰባት ዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ትርጕም ባለው መልኩ ማሳደጉንም አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል። በከተሞች የተጀመሩ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማቶችም ጽዱ እና ንጹሕ አካባቢ የመፍጠሩ አካል መኾናቸውን አመላክተዋል፡፡ ከእንጦጦ ጀምሮ የአዲስ አበባ ወንዞችን በማልማት እና በማከም አጠቃላይ የከተማዋን ተፋሰሶች የማጽዳት ተጨባጭ እንቅስቃሴ መጀመሩም ለዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ የከተማ ኮሪደር ልማቱ ወደ ተለያዩ ከተሞች ተስፋፍቶ የፍሳሽ ሥርዐቱን በማሻሻል፣ ጽዱ የመናፈሻ ቦታዎችን በመፍጠር፣ ለኑሮ ምቹ ያልኾኑ አካባቢዎችን ገጽታ በመቀየር ጽዱ ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ጥረቱን ከፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

አክለውም ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ ይዞ በመጠቀም ንጹሕ አካባቢ መፍጠር እና ንጹሕና ታዳሽ ኃይል ማመንጨት እንደሚቻል ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንደሚኾንም አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጅ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አንድ ጊዜ ተሠርቶ የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት ባለመኾኑ ማኅበረሰቡ ባህል እስኪያደርገዉ ድረስ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽኑ አጀንዳ አድርጎና ባለቤት ኾኖ እንዲሠራበት አሳስበዋል፡፡ ስለሥነ ንጽሕና እና ቆሻሻ አያያዝ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ተሞክሮዎችን በማሳየትና በማስፋት፣ የላቀ ሥራ ለሠሩት ዕውቅና እንዲያገኙ በማድረግ እንዲሁም ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጥ ዘርፉ ሚናዉን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡ የኪነ ጥበብ ዘርፉም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አስተሳሰብ የመቅረጽ ሚናዉን እንዲወጣ አቶ ተስፋሁን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Similar Posts