የፕሬስ መግለጫ
ጉባኤዉ ኢትዮጵያ ልምድ ያካፈለችበት እና የመፍትሔ አካል ኾና የቀረበችበት ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ያስተናገደችዉ 2ኛዉ የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤ ልምድ ያካፈለችበት እና ለምግብ ሥርዐት መስተካከል መፍትሔዎችን ያቀረበችበት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ እና የጣሊያን መንግሥታት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመቀናጀት ያዘጋጁት የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤ በርካታ መሪዎች፣ የግብርናዉ ዘርፍ ተመራማሪ ግለሰቦች እና ተቋማት እንዲሁም ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በታደሙበት በአዲስ አበባ ሲካሄድ ሰንብቷል፡፡ በጉባኤዉ ባለፉት ዓመታት በሥርዐተ ምግብ ለውጥ ረገድ የታዩ ስኬቶች እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ተገምግመዋል፤ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ተመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ጉባኤዉን ከማስተናገድ ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሄደችበትን ርቀት በመልካም ተሞክሮነት አካፍላለች፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በየዓመቱ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የምትተክለዉን በቢሊዮኖች የሚቈጠር ችግኝ እና ከሥርዐተ ምግብ መረጋገጥ ባሻገር ያስገኛቸዉ ውጤቶች በልምድነት ቀርቧል፡፡ ጉባኤዉ የ2030 (እ.አ.አ) የዘላቂ ልማት ግብን ለማሳካት በሥርዐተ ምግብ ረገድ ስኬት ሊመዘገብ በሚችልበት አግባብ ላይ በስፋት የመከረ፣ በርካታ አማራጭ ተሞክሮዎችን የዳሰሰ እና ቀጣይ ትኩረቶችን ያመላከተ ኾኖ ተጠናቅቋል፡፡
በሌማት ትሩፋት፣ በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በከተማ ግብርና፣ በአረንጓዴ ዐሻራ … በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበችዉ ኢትዮጵያ ከጉባኤዉ ጎን ለጎን የኹለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ግንኙነቶችን ለማጠናከር መድረኩን በእጅጉ ተጠቅማበታለች፡፡ በተጀመረዉ የማክሮ-ኢኮኖሚ ሪፎርም በግብርናዉ ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን አሳይታበታለች፡፡
ባለፈዉ በጀት ዓመት ከ150 በላይ አህጉራዊ እና ዓለማቀፍ ጉባኤዎችን ያስተናገደችዉ ኢትዮጵያ በጀመረችዉ ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ የዓለም የኮንፈረንስ ቱሪዝም የትኩረት ማእከል ኾና ቀጥላለች፡፡ የከተሞችን ገጽታ በእጅጉ መለወጧና የአገልግሎት ዘርፉ እየጎለበተ መምጣት፣ የሕዝቧ እንግዳ ተቀባይነት ባህል የዳበረ መኾን፣ ተስማሚ የአየር ንብረት ያላት መዲና ባለቤት መኾን፣ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ዐቅም እየጎለበተ መምጣት መሰል ትልልቅ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ ዕድሎችን እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
ለጉባኤዉ በስኬት መጠናቀቅ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፀጥታ ተቋማት፣ አገልግሎት ሰጪ የንግድ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም እንግዶች ለጉብኝት እና ለልምድ ለውውጥ በተንቀሳቀሱባቸዉ ኹሉ በክብር ላስተናገዱ ኢትዮጵያውያን ኹሉ መንግሥት የላቀ መስጋና ያቀርባል፡፡
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም
