የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም መስፈን በጋራ እንደሚሰሩ ተናገሩ
የአማራ ከልል መንግስትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የምክክር መድረክ ከትናንት ጥቅምት 16-17/2018 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር ከተማ ተካሄድዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዳበረ የዲሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት እና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር፣ እንዲሁም በመከባበርና በመተባበር ላይ የተመሰረተ ጤናማ የፖለቲካ ፉክክር እንዲኖር የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ባሕል ግንባታ ማስተባበሪ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ም/ል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የዳበረ ዲሞክራሲ ሥርዓት በመገንባት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የፖለቲካ ተዋኒያን የትብብርና የፉክክር ሚዛንን በመጠበቅ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓቱን የሰለጠነ ለማድረግ መስራት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተለይ የፖለቲካ ሚዛንን መጠበቅ የሚቻለዉ ሶስት ነገሮችን ማድረግ ሲቻል ነዉ ያሉት አቶ አደም፣ በሀገሪቱ ሰላምና ጸጥታ ላይ ብሄራዊ መግባባትን መፍጠር፣ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ማጠናከር እና ሀገር አቀፍ የልማት ስራዎችን በትብብር መስራት የመጀመሪያዉ ዐቢይ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የመንግስትና የህዝብ ስራዎችን እንዲያስፈጽሙ ሀላፊነት የተጣለባቸዉ አካላትም ጉልህ ድርሻ ያላቸዉ መሆኑን ያስረዱት አቶ አደም፣ በተለይ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሥርዓት ለማጎልበት የዜጎችን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በትኩረት መሰራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም በጋራ ለመስራት መተባበር እንዳለባቸዉ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም በመድረኩ ሀሳባቸዉን የሰጡ ሲሆን፣ በሀገሪቱ የዳበረ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እዉን እንዲሆን ለማድረግና ለማስፋፋት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የክልሉና የሀገሪቱን ሰላም ለማጽናት ከመንግስት ጋር በጋራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡



