ዳግም ግጭት እንዳይፈጠር የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሀብቶች፣ ምሁራን እና ኤምባሲዎች የበኩላቸዉን ሚና እንዲወጡ መንግሥት አሳሰበ፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ያስገኘዉ ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረዉ እና የክልሉ ሕዝብ ሰላም፣ ልማት እና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ ባለድርሻ አካላት ሚናቸዉን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በመገኘት ለምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ አንጻራዊ ሰላም መኖሩንና መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

“በፕሪቶሪ የተደረሰዉ የሰላም ስምምነት ለትግራይ ሕዝብ እፎታ አምጥቷል፤ ልጆቻቸዉን በየቀኑ ከማጣት ታድጓል፡፡ ለኢትዮጵያ ደግሞ ዐዲስ ባህል ፈጥሯል፤ ለካስ መንግሥት ሰላም ይበልጣል ብሎ ለተፋለሙት ኃይሎች ይሰጣል የሚል ትምህርትና ልምድ አምጥቷል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች መመለሳቸዉን እና ክልሉን የሚያስተዳድር መንግሥት መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡

የራያ እና ፀለምት አካባቢ ተፈናቃዮችወደ ቀያቸዉ መመለሳቸዉን እና የወልቃይት አካባቢ ተፈናቃዮች ግን አለመመለሳቸዉን በመጥቀስ “የወልቃይት ተፈናቃይ ወገኖቻችንም መመለስ አለባቸው” ሲሉ የመንግሥትን አቋም አሳውቀዋል፡፡ የፕሪቶሪያዉ ስምምነት አካል የኾው የትጥቅ ማስፈታት እና መልሶ ማቋቋም እንዳልተፈጸመም ገልጸዋል፡፡ የታጠቀ ኃይልን በመንግሥት በጀት ማቆየት ክልሉንም እንደሚጎዳ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእነዚህ ችግሮች የፌዴራል መንግሥቱን ተጠያቂ አድርጎ ለማሳየት መሞከር ስሕተት መኾኑን በማስገንዘብም ኹሉም ኃይሎች ኃላፊነታቸዉን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

“ለአንዳንዶች ውጊያ ጨዋታ ቢመስልም ለክልሉ እና ለሚሞቱ ወጣቶች ግን ጉዳት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግጭት መቀስቀስ ጦሱ ለቀስቃሾቹ አለመኾኑን ሕዝቡ እንዲገነዘብ አሳስበዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ በፍጹም ጦርነት እንደማይፈልግ እና ዓለማቀፍ ዓውዱም የማይፈቅድ መኾኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግጭት ቀስቃሽ ኃይሎች ተገቢ ካልኾነ ትንተና እና ወዳጅ ቈጠራ ወጥተው ነባራዊ ኹኔታዉን እንዲያጤኑም መክረዋል፡፡

በትግራይ ክልል ያለዉን ነባራዊ ኹኔታ በተመለከተ “የኹሉም ሃይማኖት አባቶች ተወካዮች ከዚህ አላችሁ! በፍጥነት ትግራይ ወደ ግጭት እንዳይባ ሥራችሁን አሁን ጀምሩ! ባለሀብቶች፣ ምሁራን፣ ኤምባሲዎች አሁን ግጭት እንዳይጀመር ሚናችሁን ተወጡ! በእኛ በኩል ጦርነት አያስፈልገንም! በሰላምና በውይይት ችግሮቻችንን መፍታት ይቻለናል!” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሳስበዋል፡፡

ከሰሜኑ ጦርነት ማግሥት መንግሥት የፕሪቶሪያዉን የሰላም ስምምነት በሙሉ ቁርጠኝነት እየተገበረ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጅ በክልሉ ያሉ ያኮረፉ ኃይሎች የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር የስምምነቱን ትግበራ ሲያጓትቱ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

Similar Posts