ፈታናዎችን በመገንዘብና የመሻገሪያ መንገዶችን ለመተለም ዜጎች ምንጊዜም ንቁ መሆን አለባቸዉ- ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
በመጪዉ ዓመት የሚኖሩ ፈታናዎችን አስቀድሞ በመገንዘብና የመሻገሪያ መንገዶችን ለመተለም ዜጎች ምንጊዜም ንቁ መሆን አለባቸዉ ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ የዘንድሮ የጷጉሜን ቀናት ስያሜን ተንተርሶ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም የተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት ሀገሪቱ ዉስብስብ ችግሮችን በመሻገር በሁሉም ዘርፎች አኩሪና እምርታዊ ድሎች ያስመዘገበችበት ዓመት እንደ ነበር አስታዉሰዋል፡፡
በመጪዉ ዓዲስ ዓመት የተገኙ ድሎች ይበልጥ የሚስፋፉበት፣ ተግዳሮቶቻችን ደግሞ የሚቀንሱበት እንዲሆን በመንግስት በኩል ሰፊ እቅድ መቀመጡን አብራርተው ይህንን መሰረት በማድረግ ወደ ንቅናቄ መገባቱን ጠቁሟል፡፡
ጷጉሜ የአዲስ ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ ተጠናቆ ስራ የሚጀመርበት፣ የክረምት ወራት አልፎ የፀደይ ወቅት ጅማሮ እና የአዲስ ዓመት ዋዜማ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ለገሰ፣ ዐዲስ ዓመት ደግሞ አዲስ እቅድ የሚተለምበት፣ አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበትና አዲስ መነሳሳት የሚፈጠርበት ወቅት ነዉ ብለዋል፡፡
የጷጉሜን ቀናት ወደ አዲስ ዓመት የሚሸጋገርበት ድልድይ እና መጪዉ እቅዶች እና ተስፋ የሚተዋወቁበት በመሆኑ ቀናቶቹ ብእጅጉ ልዩ መሆናቸዉንም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት የለዉጥ ዓመታት ቀናቶቹ በልዩ ልዩ ስያሜዎች መክበር ተለምዷል ያሉት ሚኒስትሩ፣ በአዲሱ ዓመትም ልዩ ሀገራዊ ትርጉም ባላቸዉ ስያሜዎች ለማክበር ዝግጅት መደረጉን አዉስተዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ ስያሜ በመስጠት ማክበር ያስፈለገዉ ዜጎች በአዲስ ዓመት የሀገሪቱን የልማት ፖሊሲን በአግባቡ እንደረዱ ግንዛቤ ለመፍጠር ነዉ ብለዋል፡፡
በዚህም፤ ጷጉሜን 1፣ የፅናት ቀን ሆኖ የተሰየመ ሲሆን፣ እለቱ ፅኑ መሰረት ብርቱ ሀገር በሚል መሪ ቃል የሚከበር ይሆናል፡፡
ጷጉሜን 2፣ የሕብር ቀን ሆኖ የተሰየመ በመሆኑ፣ እለቱ ብዙሃነት የኢትጵያ ጌጥ በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ይዉላል፡፡
ጷጉሜን 3፣ የእምርታ ቀን ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፣ እምርታ ለዘላቂ ከፍታ በሚል መሪ ቃል ተሰይሟል፡፡
ጷጉሜን 4፣ የማንሰራራት ቀን ሆኖ የተሰየመ ሲሆን፣ ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሰራራት በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል፡፡
ጷጉሜን 5፣ የነገዋ ቀን ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፣ ዲጂታል ኢትዮጵያን እዉን ማድረግ በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡
