1ኛው የአፍሪካ የከተሞች ፎረም ሁለተኛው ቀን ውሎው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀችው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም “ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063” በዓድዋ መታሰቢያ ፓን-አፍሪካን አዳራሽ በሁለተኛ ቀን ውሎው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እየመከረ ነው፡፡
በፎረሙ ላይ የተባበሩት መንግስታት የሥራ ኃላፊች፣ የዓለም ዓቀፍ የልማት ድርጅቶች፣ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና የተቋማት ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ ከተማ ከንቲባዎች፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎች፣ የግሉ ሴክተር አንቀሳቃሾች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት ኤጀንሲዎች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአህጉሪቱ የከተማ ልማት እና ቀጣይ እቅድ ዙሪያ እየተወያዩ ነው፡፡
በውይይታቸውም የአፍሪካ ከተሞች ተገቢውን የከተሜነት ደረጃን ማሟላት እንዲችሉና ለኑሮ ምቹ፣ ተመራጭና ሰላማዊ ለማድረግ እንዲሁም እየጨመረ የመጣውን የከተሜነት ምጣኔ ለመቆጣጠር በሚቀረፁ ፖሊሲዎች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ፡፡
በውይይቱም የተለያዩ ሃሳቦች ቀርበው እየተመከረባቸው ሲሆን እ.ኤ.አ በ2015 በአፍሪካ ከተሞች የነበረው የነዋሪዎች ቁጥር ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከፍተኛ መጠን እያደገ መምጣቱ ተመላክቷል፡፡
1ኛው የአፍሪካ የከተሞች ፎረም ለዚህና ሌሎች ፈተናዎች መፍትሄዎችን ሊያመነጭ እንደሚገባም ተነስቷል፡፡
በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው 1ኛው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ነገም ቀጥሎ ይውላል።
