የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትናንትናው እለት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ ሐምሌ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ስርአት መቆጣጠር እንደማይቻል በመግለጽ ለፌዴራል መንግስት ጥያቄ ማቅረቡን አስታውሰዋል፡፡ ይህን ተከትሎ መንግሥት ሰላምን፣ የሃገር ደህንነትን እንዲሁም ሕገ መንግስታዊ ስርአትን የማስከበር ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ በክልሉ የሚታየውን ሕገ ወጥ የትጥቅ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የክልሉ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
በዚህም መሰረት ከትናንት ጀምሮ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋል መጀመሩን ሚኒስትሩ ጠቁመው ሁሉም ዜጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ክልከላ የጣለባቸውን ድርጊቶች ባለመፈጸም ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊነት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ባለፈው ዓመት በሰሜኑ ጦርነት የደረሰበትን ጉዳት በሚያካክስ መልኩ ዘንድሮ በልዩ ትኩረት በክልሉ የእርሻ ሥራ መጀመሩን ሚኒስትሩ ጠቁመው ነገር ግን የታጠቁ ዘራፊ ቡድኖች ለአርሶ አደሩ የግብርና ግብአት በወቅቱና በአግባቡ እንዳይደርስ መንገድ በመዝጋትና ዘረፋ በመፈጸም ሥራዎችን እየተስተጓጎሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ክልሉ ባለፈው ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የተጎዳ እንደነበር ዶክተር ለገሰ አስታውሰው አሁን በክልሉ ሰላምን እያወከ ያለው ዘራፊ ቡድን መንገድ በመዝጋት፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ስም በማጥፋት፣ ካምፖችን በመክበብና በመተንኮስ ተግባር ላይ ተሰማርቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊታችን የኢትዮጵያ ደጀንና ኩራት መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ መከላከያው በሰሜኑ ጦርነት ከማንም ቀድሞ ለአማራ ሕዝብ የደረሰ ሕይወቱን ሰጥቶ ለሕዝብ ደራሽነቱን ያሳየ መሆኑን ጠቁመው መንግስት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በማደረግ ክልሉን ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል ያለውን ችግርም በሃገር ሽማግሌዎችና በተለያዩ በክልሉና በፌዴራል አካላት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረጉት ጥረቶች ሊሳኩ ስላልቻሉ መንግስት ወደ ሕግ ማስከበሩ መግባቱን አንስተዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱንና ይህ አዋጅም ለስድስት ወራት ጸንቶ የሚቆይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አዋጁ በዋናነት በአማራ ክልል ተግባራዊ እንደሚሆን የተናገሩት ዶክተር ለገሰ ነገር ግን የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከየትኛውም ክልል አዋጁን የሚጻረር ድርጊትና ትንኮሳ ካለ አዋጁ ተፈጻሚ ይሆናል ብለዋል፡፡

Similar Posts