የፌዴራል ፖሊስ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ስርዐት ያደረገው ሪፎርም

በ1913 በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ዘመን የኢትዮጵያ ፖሊስ በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተመሠረተ። በ1963 ከጣሊያን ወረራ በፊት የመዲናዋን ፀጥታ ለማስጠበቅ የተቋቋመዉ የፖሊስ ሃይሉ “የከተማ ዘበኛ” በመባል ይታወቅ ነበር። የቀድሞ የከተማ ዘበኛ የአሁኑ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እራሱን አዘምኖና ተጠናክሮ ከምንጊዜውም በላይ ለዜጎች ደህንነት እየሰራ ይገኛል። የወንጀል ድርጊት ከዘመኑ ጋር እየረቀቀና እየተወሳሰበ በመምጣቱ ይህን ለመከላከልና ለመመርመር የሚያስችል አቅም መፍጠር አማራጭ የሌለዉ በመሆኑ የወንጀል ምርመራና መከላከል፣ የትምህርት ስልጠና እንዲሁም ሌሎች የፖሊስ ተልዕኮዎች ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂዎች እንዲታገዙ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠዉ በመሆኑ እንደ አንድ የሪፎርሙ ቁልፍ ሲሰራበት ቆይቷል።
ባለፉት ስድስት አመታት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ስርዓት ተሸጋግሯል። የፌዴራል ፖሊስ ዲጂታል ሪፎርም ስራዎች ዜጎች በወንጀል መከላከል ስራ ይበልጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ እድል የፈጠሩ ናቸው። ግንቦት15/2016 ዓ.ም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የዜጎችን ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp) ያስጀመረ ሲሆን ይህ ስራ ለዜጎች መሰረታዊ አገልግሎት ለመስጠት ታልሞ የሚከናወነው የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ አካል ነው። የህዝብ ብዛት እየጨመረ ባለበት ከተማችን ንቁ የዜጎች ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው። ወደ ስራ የገባው መተግበሪያ ዜጎች ወንጀልን ለመከላከል በፎቶግራፍ፣ በቪዲዮ፣ በድምፅ፣ በሰነድ ወይም በቀጥታ በመደወል ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያስችላል።
