“መንግስት ምርትን በብዛትና በጥራት በማምረት የተያዘዉን በምግብ ራስን የመቻል ግብ እዉን እያደረገ ይገኛል”

-አቶ ከበደ ዴሲሳ-የመንግስት ኮሙኒኬሽ አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ
መንግስት ምርትን በብዛትና በጥራት በማምረት እና የአርሶ አደሩን ኑሮ የሚቀይሩ ስራዎችን በመስራት የተያዘዉን በምግብ ራስን የመቻል ግብ እዉን እያደረገ እንደሚገኝ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ገለጹ፡፡
በኢፌድሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪነት ህዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ቡድን በአርሲ ዞን ሌሙና ብልብሎ ወረዳ ዉስጥ እየተሰሩ ያሉ አጠቃላይ የልማት ስራዎችን ተዘዋውሮ ምልከታ አድርጓል፡፡ በዚህም የወረዳዉ ወተት አምራች ማህበርና በክላስተር የለማዉን የቢራ ገብስን ማየት ተችሏል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ በዚህ ወቅት እንደ ገለጹት፣ መንግስት ምርትና ምርታማነትን በብዛት በማምረትና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተያዘዉን በምግብ ራስን የመቻል ግብ እዉን እያደረገ ይገኛል፡፡ አርሶ አደሮችም ኑሮኣቸዉን ከማሻሻል ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ በቂ ምርቶችን ለገቢያ እያቀረቡ እንደሚገኙ አብራርቷል፡፡ ለዚህም በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ዉስጥ የደረሱ የስንዴና የገብስ ሰብሎችን ለአብነት ጠቅሷል፡፡
መንግስት የሚከተለዉ የፖሊሲ ማዕቀፍ በሁሉም መስኮች ራስን መቻል ነዉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዉ፣ በምግብ ራስን ለመቻል በብዛት ማምረትና ምርታማነትን መጨመር ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሰራበት ቆይቷል፤ አመርቂ ዉጤትም አስገኝቷል ብሏል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የሰብል ምርቶችን በብዛት በማምረት ከዉጭ ሲገዙ የነበሩ ምርቶችን ኢዚሁ ሀገር ዉስጥ ማምረት መቻሉን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዉ፣ በተለይ ለቢራ ፋብሪካዎች ከዉጭ ተገዝቶ ሲገባ የነበረ የቢራ ገበስ ሀገር ዉስጥ ማምረት መቻሉን አብራቷል፡፡ ይህ ደግሞ የዉጭ ምንዛሪን ማዳን ችሏል ብሏል፡፡
ሀገሪቱ ሰፊ የለማ መሬት እና ማምረት የሚችል በቂ የሰዉ ሀብት አላት ያሉት አቶ ከበደ፣ አሁንም ድረስ ከዉጭ የሚገቡ ምርቶችን ለማስቀረት ተኪ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ማምረት፣ እንዲሁም መንግስት የምርት አቅርቦት ስራን ለማሻሻል በትኩረት እየሰራበት እንደሚገኝ ጠቅሷል፡፡
