ኢትዮጵያ እና ቻይና እውነታቸዉን በላቀ ደረጃ የሚገልጹበትንና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉን ትስስር ለማጎልበት ያለመ የሁለትዮሽ ውይይት አካሄዱ፡፡

ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና የቻይናዉ ብሔራዊ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን አስተዳደር በጋራ በሚሠሩባቸዉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል፡፡ የቻይና ልዑካንን የመሩት ሚስ ሳዎ ሹሚን በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) እና ከተቋሙ ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር በመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ጽ/ቤት ተወያይቷል፡፡

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የተሻገረዉን የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና ዲጂታል ሚዲያ የበለጠ ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ነው ልዑካኑ የመከሩት፡፡

ዘመን ተሻጋሪ እና ኹኔታዎች ያልገደቡት ወዳጅነት ያላቸዉ ኢትዮጵያ እና ቻይና ስኬቶቻቸዉን እና እውነቶቻቸዉን ለዓለም የበለጠ የሚገልጹበት የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ወደላቀ ትብብር በሚያድግበት ዙሪያ አተኩረው መክረዋል፡፡

ጥራት እና ጥልቀት ያለው ይዘት በማዘጋጃት እና በጋራ ተደራሽ በማድረግ የሀገራቱን እውነትና ስኬት መግለጽ፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉን ዐቅም በቴክኖሎጂ ማዘመንና በሰው ኃይል ዐቅም ማላቅ፣ የልምድ ልውውጥ በማድረግ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትንና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉን መስተጋብር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር፣ በትምህርት እና ሥልጠና ዘርፎች በትብብር መሥራት በምክክሩ ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ባለው መልካም ግንኙነት ከ288 የሚዲያ ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት ወደ ቻይና በማቅናት ልምድ መቅሰማቸው እና ሥልጠና ማግኘታቸው በውይይቱ ተመላክቷል፡፡ ይህንን በማጠናከር ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ያደገዉን የሁለቱን ሀገራት ትብብር ለማጎልበት እንደሚሠሩም ልዑካኑ ተግባብተዋል፡፡

Similar Posts