ኢትዮጵያዊነት በኅብር ቀለም!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያዊነትን የገለጹበት መንገድ የመደመር ፍልስፍና መሠረት ሲሆን ኢትዮጵያዊነትን በአንድ ወገን ወይም በአንድ ቀለም ሳይሆን፣ በሁለንተናዊ የኅብረት ስብስብ መልክ አስቀምጠዋል።

“ኢትዮጵያዊነት በኅብር ቀለም የሚሳል፤ በኅብር ባህል ሚኖር፤ በኅብር ቋንቋ የሚነገር፤ በኅብር ደም የተሠራ፤ በኅብር ላብ የሚገነባ፤ በኅብር ጥበብ የሚሻገር” የሚለው ሐሳብ፣ ብዝኃነትን እንደ ስጋት ሳይሆን እንደ ጥሬ ኃይል (Raw Power) ያሳያል።

እያንዳንዱ የባህል፣ የቋንቋና የጉልበት ልዩነት ለሀገር ግንባታ የሚውል የጋራ ሀብት መሆኑን ያሰምርበታል።

“ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ የነበሩ፣ የሚኖሩ የሚጸኑ፣ የማይናወጡ መሆናቸውን ዳግም በኩራት ለመላው ኢትዮጵያውያን እገልጻለሁ” የሚለው መልእክት፣ ሀገሪቱ በውስጥና በውጪ ጫና ውስጥ በምትገኝበት ወቅት የብሔራዊ ማንነት ዘላለማዊነትና የማይፈርስ መሠረት እንዳላት የሚያረጋግጥ የፅናትና የመተማመን መልእክት ነው።

የመደመር እሳቤ ለፍትሃዊ ብልጽግና፣

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የብዝኃነትን ዕውቅና ከፍትሃዊነትና ከእኩልነት ጋር ያያይዘዋል።

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቁጥር ወይም በኢኮኖሚ ብቃት ሳይለያዩ እኩል በመደመር፣ ብልጽግና ለጋራ ዓላማ እንዲውል ማድረግ የዚህ ትውልድ ቁልፍ ተግባር ነው።

ነፃነትንና ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ የአባቶች የደም ውርስ ሲሆን፣ ይህንን ውርስ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ደግሞ የዛሬው ትውልድ ግዴታ ነው።

“በአባቶቻችን ደም የወረስነውን ነጻነት በብልጽግና ማጽናት ከዚህ ትውልድ የሚጠበቅ ተግባር ይሆናል” የሚለው ሐሳብ፣ ሉዓላዊነትን በመጠበቅ ላይ መደላደል ሳይሆን፣ ያንን ሉዓላዊነት ኢኮኖሚያዊ ትርጉም ያለውና በልማት የተረጋገጠ ማድረግ የትውልዱ ትልቁ ድል መሆኑን ያሳያል።

“የጀመርነውን ለመጨረስ፣ ያልጀመርነውን ለመጀመር፣ ኢትዮጵያን ለማጽናት በጋራ እንድንቆም” የተላለፈው ጥሪ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በዲፕሎማሲ እና በመሠረተ ልማት ዘርፎች የተጀመሩትን የልማት ፕሮጀክቶች በቁርጠኝነትና በአንድነት ማሳካት እንደሚገባ የጠነከረ የተግባር ጥሪ (Call to Action) ነው።

አንድ ክር ደካማ ነዉ፤ ብዙ ክር ግን የማይበጠስ ገመድ ነዉ፡፡ ስንበዛና ስንሰናሰል በቀላሉ የማንበጠስ ጠንካራ ገመድ እንሆናለን፡፡ 

መተባበር፤ መከባበር፤  በጋራ መቆም ፤ብሄራዊ ጥቅምን ማስቀደም የሁላችንም ሃብትና ስንቅ ሊሆን ይገባል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፣ የብሔሮች ብሔረሰቦች ቀን የሕገ መንግስትና የፌዴራል ሥርዓት ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን፣ የብሔራዊ አንድነትና የጋራ ብልፅግናን ራዕይ የሚያስተጋባ መድረክ መሆኑን አሳይቷል።

ኢትዮጵያን ለማጽናት እና ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር ቁልፉ በኅብር ቀለም፣ በወንድማማች ዐይን ተያይቶ በመደመር መቆም መሆኑን አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

Similar Posts