የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት እና አንድምታዉ

“ከአንበሶች ግዛት እስከ አንበሶች ምድር” የጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ታሪካዊ የፓርላማ ንግግር”

ኢትዮጵያና ሕንድ እንደ ሀገር ግንኙነት ከመሰረቱበት ጊዜ ጀምሮ በንግድ፣ በልማት እና በባህል ልውውጥ ዘርፎች ላይ በመተባበር ጥብቅ ወዳጃዊ ግንኙነት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ሁለቱ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን እና የደህንነት ጉዳዮችን ጨምሮ በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ አንዳቸው የሌላውን ጥቅም ሲደግፉም ቆይተዋል። በኢትዮጵያና በሕንድ መካከል እየዳበረ የመጣው አጋርነት ታሪካዊ ትስስርን፣ የጋራ መተማመንን እና ለብልጽግና የወደፊት ተስፋ ያላቸውን የጋራ ምኞት አስፈላጊነትን ያሳያል። ሁለቱም ሀገራት በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎ እያጠናከሩ ሲሄዱ፣ ለጋራ እድገት ያላቸው አቅም እጅግ ከፍተኛ ሆኖ ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ፓርላማ የጋራ ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያን የአንበሶች ምድር በማለት የጠሩት ሲሆን፣ የትውልድ ግዛታቸው ጉጃራትም የአንበሶች መገኛ በመሆኑ ኢትዮጵያም እንደ ቤታቸው እንደሆነች እንደሚሰማቸው ገልጸዋል፡፡ ሞዲ በንግግራቸዉ ወቅት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና በሕንድ የታሚል ናዱ የድንጋይ ፍልፍል ቤተመቅደሶች ያላቸውን ተመሳሳይነት በማንሳት የሁለቱን ሀገራት ጥንታዊ ስልጣኔዎችን በማንጽር ወዳጅነታችን ጥንታዊ ነው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡

ናሬንድራ ሞዲ ኢትዮጵያና ህንድ ለሰላምና ለሰው ልጅ ደህንነት የቆሙ የዲሞክራሲ ሃይሎች እንዲሁም ደቡብ-ደቡብ (South-South Cooperation) ትብብር አጋሮችና አብሮ ተጓዦች መሆናቸውን ገልጸዋል። (South-South Cooperation) ማለት በማደግ ላይ ባሉ የዓለም ሀገራት (በተለምዶ “Global South” በሚባሉት) መካከል የሚደረግ የቴክኒክ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የባህል ትብብር ነው። በዚህ መሠረት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በነበራቸው ቆይታ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት (Strategic Partnership) ለማሳደግ መወሰናቸውን በአጽንኦት አስታዉሰዋል። ይህም በቴክኖሎጂ፣ በኢኖቬሽን፣ በማዕድን እና በታዳሽ ኢነርጂ ዘርፎች ትብብርን ለማጠናከር ይረዳል ያሉ ሲሆን ይህ ትብብር ሀገራቱ ዕርስ በዕርሳቸው እውቀትን፣ ክህሎትን፣ ቴክኖሎጂንና ግብዓቶችን በመለዋወጥ የጋራ የልማት ግቦቻቸውን እንዲያሳኩ የሚያግዝ ነው::

ሞዲ አሁናዊ የህንድ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሸጋገሩን ገልፀው ይህ ርምጃ ለግንኙነታችን አዲስ ጉልበት፣ አዲስ ፍጥነት እና አዲስ ጥልቀት ይሰጣል በማለት የኢትዮጵያና ሕንድ ግንኙነት በአዲስ ምዕራፍ መጀመሩን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸው በቀጣይ በግብርናው ዘርፍ የተሻሻሉ ዘሮችን፣ የመስኖ ሥርዓቶችን እና የአፈር ጤና ቴክኖሎጂዎችን ሕንድ ለኢትዮጵያ ለማጋራት ፍለጎት አላት ብለዋል ፡፡ይህም የሕንድና የኢትዮጵያ ወዳጅነት አብሮ በማደግ ላይ የተመሰረተ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሆኑን ያሳያል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የኢትዮጵያን አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ከሕንዱ “Ek Ped Maa Ke Naam” (አንድ ዛፍ ለእናቴ) ተነሳሽነት ጋር በማነጻጸር፣ ሁለቱም ምድርን እንደ እናት በመንከባከብ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ዓለምን ለማስረከብ ያለሙ ናቸው ብለዋል። ሕንድ በታዳሽ ኃይል፣ በአረንጓዴ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል። በአጠቃላይ ሞዲ አረንጓዴ ዐሻራን እንደ አንድ ትልቅ “የሀገር ግንባታ እና የተስፋ ተምሳሌት” አድርገው የተመለከቱት በመሆኑ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በዘርፉ ትክክለኛ መንግድ ላይ እንዳለች አመላካች ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕንድ መምህራን በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ውስጥ የነበራቸውን ታሪካዊ ሚናን በተመለከተ “የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመጀመሩ በፊትም ቢሆን ህዝቦቻችን ግንኙነት ነበራቸው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የሕንድ መምህራን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከአዲስ አበባ እስከ ድሬዳዋ፣ ከባህር ዳር እስከ መቐለ ባሉ ትምህርት ቤቶች አስተምረዋል በማለት የቀደመዉን የሁለቱን ህዝቦች ግንኙት ምንያህል ጥልቅ እንደሆነና ለአሁኑ አጋርነት መሰረት እንደጣለ አስታዉሰዋል፡፡

ሞዲ ይህ ታሪካዊ ግንኙነት ዛሬም እንደቀጠለ እና ወደፊትም እንደሚጠናከር በማግለጽ ሕንድ ለኢትዮጵያ ተማሪዎች የምትሰጠውን የነፃ ትምህርት ዕድል (Scholarships) እና የአጭር ጊዜ ሥልጠናዎችን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። የቴክኖሎጂ ሽግግር በተመለከተም በትምህርት ዘርፍ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ትብብር ለማድረግ እና ዕውቀትን ለማጋራት ሕንድ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

ሞዲ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ስትራቴጂካዊ ቦታ እና ሕንድ በሕንድ ውቅያኖስ መካከል ያላትን ስፋት በማነጻጸር ሁለቱ ሀገራት ለቀጣናዊ ሰላምና ደህንነት ተፈጥሯዊ አጋር መሆናቸውን ገልጸዋል። በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ የተፈረመውን የመከላከያ ትብብር ስምምነት (Defense Cooperation Agreement) እንደ ትልቅ ስኬት ማሳያ ጠቅሰውታል ይህ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መከላከያ ያለውን ግንኙነት ማጠናከር፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ጥቃትን በጋራ መከላከል፣ በመከላከያ መሳሪያዎች ምርምር እና ልማት ዙሪያ በጋራ መስራት እና ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ስልጠና እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ማድረግ እንደሆነ በንግግራቸዉ ወቅት አስታዉሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽብርተኝነትን “ዜሮ (Zero Tolerance) ማድረግ እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለፁት ፡- ሕንድ በአፍሪካ መሪነት ለሚከናወኑ የልማት አጋርነት የምትሰጠውን ትኩረት አድንቀው፤ ይህ አካሄድ ኢትዮጵያ ‘በአፍሪካውያን ባለቤትነትና በአፍሪካውያን ለሚመራ የልማት ራዕይ ካላት አቋም ጋር የሚጣጣም መሆኑን ገልጸዋል።

የተለያዩ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት፤ የኢትዮጵያና የህንድ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለሁለቱም ሀገራት ዘርፈ-ብዙ ፋይዳዎችን ያስገኛል። ከነዚህም መካከል የቀይ ባሕርና የአፍሪካ ቀንድ ያለውን ስልታዊ መልክዓ-ምድራዊ ጠቀሜታ ለጋራ ደህንነት ማዋል፣ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ድምፅ ለማጎልበት የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ማጠናከር፣ እንዲሁም ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ የጋራ ግቦችን በስኬት ማሳካት ናቸው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያና ህንድ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ሰፊና አካታች በሆነ መንገድ ለማጠናከር እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ጉልህ ለውጥ ለማምጣት በጋራ ለመስራት ተዘጋጅተዋል ማለት ይቻላል፡፡ “ድር ቢያብር አንበሳን ያስር” የሚለውን የኢትዮጵያውያን አባባል በመጥቀስ፣ የሕንድ እና የኢትዮጵያን አቻዊ ወዳጅነት ለማጠናከር ቃል በመግባት ንግግራቸውን አጠቃለዋል፡፡

ተጨማሪ መረጃ

https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication

Similar Posts