ኢትዮጵያ እምቅ አቅሟን እና ታላቅ ርዕይዋን የሚመጥን ሌላ ተጨማሪ ሜጋ ፕሮጀክት ጀምራለች።
የቢሾፍቱ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ይሆናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የአውሮፕላን ማረፊያውን ግንባታ ይፋዊ በሆነ መርሃ ግብር ዛሬ በስፍራው አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እለቱ ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊነት እና ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ አንድ እጥፋት ነው በማለት ገልጸውታል። የኢትዮጵያ አየር መንገድም የሀገር የኩራት ምንጭ መሆኑን አውስተው ይኽ የሆነው ግን ያለተግዳሮት በመጓዙ ሳይሆን በጽናት በተሞላው እንቅፋቶችን የመሻገር አቅሙ እና በአፍሪካ የፋና ወጊነት ሚናው የተነሳ መሆኑን ገልጠዋል። የአየር መንገዱ ትልቁ ጥንካሬ የሚመነጨው ከጠንካራው ተቋማዊ ባሕሉ የሚመነጭ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል። ይኽም በሚከተሉት ላይ የተገነባ መሆኑን ገልጠዋል:-
– ለጥንቃቄ እና ደኅንነት ቅድሚያ መሥጠት
– በፈጠራ እና ጠንካራ ሥራ የሚመራ አመራር
– ከ26,000 በላይ ቁጥር ያለው በአየር መንገዱ ሰንደቅ ተሸካሚነት እና የሚወክለውን የሚያምኑ እና የሚያከብሩ ሠራተኞች
– ያላሰለሰ የመማር እና የአቅም ግንባታ ጥረት
ከአዲስ አበባ ደቡብ ምዕራብ በ40 ኪሎሜትር ርቀት በ1910 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ቢሾፍቱ ለአውሮፕላኖች የተመቸ ከባቢ ብሎም ኢትዮጵያን መዳረሻ ለሚያደርጉም ሆነ ለትራንዚት መንገደኞች ምቹ አቀባበል የተመቸች ያደርጋታል። ፕሮጀክቱ ብዛት ያላቸው የተሽከርካሪ መስመሮችን የያዘ አዲስ አበባን ከአዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ የሚያገናኝ ዘመናዊ መንገድ ግንባታን ያካተተ ሲሆን በሰዓት ከ120-200 ኪሎሜትሮች ፍጥነት ያለው የከፍተኛ ፍጥነት የባቡር ሀዲድ እና ሥርዓት ግንባታንም አካትቷል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የቢሾፍቱ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማስተናገድ የሚችል ሲሆን በታቀደው መሠረት ሙሉ ግንባታው በሚጠናቀቅበት ወቅትም በአመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ያስተናግዳል። ይኽም ኢትዮጵያን ከአለም ግንባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት ማዕከላት አንዷ ያደርጋታል።
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/FDREGovermentCommunication















